የክልሉ መንግስት የሕዝቡን ጥቅም በማስከበር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ይሠራል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

65
የካቲት 10/2012 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት የሕዝቡን ጥቅም በማስከበር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡ አቶ ሽመልስ ይህን ያሉት የክልሉን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለጨፌ ኦሮሚያ ባቀረቡበት ወቅት ነው። የክልሉ መንግስት የሕዝቡን ፍላጎት፣ መብትና ጥቅም በማስከበር የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ከአዋሳኝ ክልሎች ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር በትኩረት እየሰራ መቆየቱን ገልፀዋል። በግብርና ልማት የክልሉን የቡና ልማት ዘርፍ አቅም ለማሳደግ 147 ሚሊዮን ብር በመመደብ አሲዳማነት የተገጎዱ   10 ዞኖችና 75 ወረዳዎች  አፈርን በማከም  የቡና፣ ሻይና አቮካዶ ልማት መከናወኑን ተናግረዋል። ለውጭ ገበያ ለሚቀርቡ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ልማት ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱንም አስታውቀዋል። ለግብርና ሜካናይዜሽን ብድር የሚውል የ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር መቅረቡን ያወሱት አቶ ሽመልስ 350 ትራክተሮችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በአነስተኛና ጥቃቅን ለተደራጁ 142 ማኅበራት በብድር መሰጠቱን ጠቁመዋል። በመንገድ ልማት ዘርፍም 203 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የጠጠር ማልበስ ስራ መሰራቱን፣ 218 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መንገድ ስራ ተጠናቆ አገልግሎት መጀመሩን እንዲሁም የ3 ሺህ 144 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና መካሄዱን ዘርዝረዋል። ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት የመዘርጋትና ህገወጥ የመሬት ወረራን የመከላከል ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል። በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ 66 በመቶ የነበረውን የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት በ2012 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ወደ 74 በመቶ በማሳደግ ተጨማሪ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ከ365 ሺህ በላይ ሰዎች ቋሚ፣ ከ174 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ጊዜያዊ፤ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። እንደ አቶ ሽመልስ ማብራሪያ የስራ ዕድል ፈጠራው ከተያዘው ዕቅድ አንፃር ሲታይ 98 በመቶ ማሳካት ተችሏል። በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 11 ነጥብ 53 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 11 ነጥብ 89 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለና ይህም ከዕቅዱ 104 በመቶ እንደሆነ ተናግረዋል። በጨፌው የሁለት ቀን ጉባዔ ቆይታ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችና ሹመቶች ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ይፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጉባዔው በሕግ የበላይነትና በክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ላይ በትኩረት እንደሚመክርም ተገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም