ኢትዮጵያና ቻድ ለትምህርት ዘርፍ የሚውል 48 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኙ  

62
 የካቲት 10/2012 (ኢዜአ) ኤዱኬሽን ካንኖት ዌይት  የተሰኘው ድርጅት  የኢትዮጵያንና የቻድን ትምህርት ዘርፍ ለመደገፍ የሚውል  የ48 ሚሊዮን ዶላር መደገፉን አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ በመጪዎቹ ሶስት አመታት በሀገራቱ የትምህርት ዘርፍ የሚታዩትን ቁልፍ ችግሮች  ለመፍታት  ቅድሚያ እሰጣለሁ ሲል ይህን ለማስፈጸምም 48 ሚሊዮን ዶላር  መበጀቱን አስረድቷል ፡፡ ፕሮግራሙ ረጅም አመት እንደሚወስድ የታቀደ ሲሆን ለተግባራዊነቱ በአጠቃላይ 216 ሚሊዮን ዶላር ተበጅቷል፡፡ ይህም በዋናነት በትምህርት ጥራት ላይ በማተኮር አንድ ሚሊዮን ገደማ ህጻናትና ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ ፕሮግራሙ በድርቅ ፣በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግጭቶች እና በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው መማር ያልቻሉት ዜጎች ቅድሚያ መስጠቱን  ጠቁሟል፡፡ መርሀ ግብሩ በኢትዮጵያና ቻድ  በቅድሚያ ቢተገበርም በቀጣይ በተለያዩ ቀውሶች ለተጎዱ አገራት እንደ አፍጋኒስታን፣ ፍልስጤም፣ ባንግላዴሽ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣፣ ሶማሊያ እና ሶሪያ ይቀጥላል ነው የተባለው፡፡ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ያስሚን ሸሪፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፣ ፕሮግራሙ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ቀውስ  የተጎዱ አካባቢዎች ለሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት  እንሰራለን ብለዋል፡፡ ከተባበሩት መንግስታት፣ ከተራድኦ ድርጅቶች እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽነትን ለማሳካት አንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡ በቻድ በመጀመሪያዎቹ ሶስት አመታት በ21 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በሚተገበረው ፕሮግራም ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ 230 ሺ ሴቶችና ወንዶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ሆኖም ተግባሩን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ተጨማሪ 30 ሚሊዮን ዶላር ሊያስፈልግ አንደሚችልም ተገምቷል፡፡ በተመሳሰይ በኢትዮጵያም በ27 ሚሊዮን ዶላር መነሻነት 746ሺ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ አንደሚሰራ የተነገረ ሲሆን ፕሮግራሙ ግቡን እንዲመታ ግን 165 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ በቻድ 1.2 ሚሊዮን ህጻናት በተለያዩ ቀውሶች ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ደግሞ በተፈጥሮ አደጋዎችና በግጭቶች ምክንያት 728 ገደማ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን አፍሪካን ቢዝነስ  ኮሚዩኒቲ አስነብቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም