ወደ ብልፅግና የሚያደርገውን ጉዞ እንዲሳካ የሚደግፉ መሆናቸውን በኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ

177

መቱ፣ የካቲት 10/2012 (ኢዜአ) ሀገሪቱ ወደ ብልፅግና የምታደርገው ጉዞ እንዲሳካ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በኢሉአባቦር ዞን የያዮ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ይህንን የገለጹት በወረዳው ዋና ማዕከል ያዮ ከተማ ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ ላይ ባነገቧቸው መፈክሮችና በሰጡት አስተያየት ነው።

“ከብልፅግና ጋር መንገዳችን ብሩህ ነው፣ የብልፅግና ፓርቲ የብሔር ብሔረሰቦችን በማቀፍ ወደ ብልፅግና የሚያደርገውን ጉዞ እንደግፋለን፣ የኦሮሞ ህዝብ በአካባቢ ለመከፋፈል የሚጥሩ አካላትን እናወግዛለን እና በዶክተር አብይ አመራር ሰጪነት የተመዘገበውን እና አለም ያደነቀው ለውጥ እንዳይደናቀፍ እንሰራለን” የሚሉ መፈክሮች ነዋሪዎቹ ካነገቧቸው መካከል ይገኙበታል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል የያዮ ከተማ ወጣት ኤሊያስ ለሜሳ በሰጠው አስተያየት ከረጅም ዓመታት በኋላ ከስደት ወደ ሀገር ገብተው በነፃነት መንቀሳቀስ የጀመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዲሞክራሲና መቻቻልን ከለውጥ አመራሩ መማር እንጂ ማደናቀፍ እንደሌለባቸው ተናግሯል።

በሀገሪቱ ከለውጡ ወዲህ የተረጋገጡ የመናገርና ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች በእድሜዬ አይቼ አላውቅም ያለው ወጣቱ ለውጡ ሀገሪቱን ወደ ብልፅግና የሚያሸጋግር በመሆኑ በመደገፍ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

ወጣት አንዋር ሲራጅ  እንደገለጸ የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሞ ህዝብን አንድነት በማጠናከር እና የብሔር ብሔረሰቦችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማረጋገጥ እየሰራ ያለው ስራ መበረታታት አለበት።

የያዮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጅሐድ ናስር ለሰልፈኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት የሀገሪቱን የረጅም ግዜ ችግሮች በመፍታት ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር ለጀመረው ጉዞ ለማሳካት ህብረተሰቡ በመደገፍ ማጠናከር አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

በመደመር ተከባብሮና ተፋቅሮ በጋራ መኖር የኦሮሞ ህዝብ አኩሪ እሴቶች በመሆናቸው ይህንን በማጎልበት ሀገሪቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገር መስራት እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ረጋሳ ናቸው።

በድጋፍ ሰልፉ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮች ጨምሮ በወረዳው የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ተሳታፊዎቹም የድጋፍ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ መረሀ ግብራቸውን አጠናቀው ወደየመጡበት በሰላም ተመልሰዋል።

በተጨማሪም በዚሁ ዞን የዶረኒ ወረዳ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ዛሬ የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል።