በንግዱ ዘርፍ ፈጣን፣ ፍትሃዊና ከአድሎአዊነት የጸዳ አገልግሎት ማስፈን ያስፈልጋል ተባለ

63
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 የንግዱ ዘርፍ ለአገሪቷ ምጣኔ ሃብት እድገት ያለውን ፋይዳ ለማጎልበት ፈጣን፣ ፍትሃዊና ከአድሎ የፀዳ አገልግሎት ለመፍጠር መረባረብ እንደሚገባ የንግድ ሚኒስቴር አሳሰበ። ይህም በሀገሪቱ ሚዛናዊና ጤናማ የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር ብሎም መንግስትና ህዝብ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል። የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በአገሪቱ ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፐብሊክ ሰርቪስ ቀን ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል። በዚሁ ጊዜ በሚኒስቴሩ የንግድ አሰራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኃብታሙ ሲሳይ እንደገለፁት የመስሪያ ቤቱ አመራሮችና  ሰራተኞች የንግዱ ዘርፍ ለአገሪቷ ምጣኔ ኃብት የሚያበረክተውን አስተዋጾኦ ተገንዝበው ለውጤታማነቱ መትጋት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ መንግስት በየጊዜው ከሚወስዳቸው ማሻሻያዎች በተጓዳኝ የሚኒስቴሩ አመራሮችና ሰራተኛው ፈጣን፣ ፍትሃዊና ከአድሎ የጸዳ አገልግሎት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውም አቶ ኃብታሙ አሳስበዋል። ይህም የንግዱ ማህበረሰብ የሚገጥመውን ችግር ለመቅረፍ፣ በንግዱ ማህበረሰብና በሸማቹ ህዝብ መካከል ሚዛናዊና ጤናማ የንግድ ግንኙነት እንዲኖር እንደዚሁም መንግስትና ህዝብ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል። የንግዱ ማህበረሰብ እርካታን ለማረጋገጥ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆኑን አቶ ሃብታሙ ጠቅሰው በቀጣይም የሚኒስቴሩን አሰራር ለማዘመንና የሰራተኛውን አቅም ለመገንባት እንደሚሰራም አብራርተዋል። የበዓሉ ተሳታፊ ሰራተኞች በበኩላቸው የሚኒስቴሩን አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግና የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ አደረጃጀቶችን የማሻሻል፣ የዜጎች ቻርተርን በተገቢው መተግበርና ቅሬታዎችን በወቅቱ መፍታት ተገቢ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። አቶ እንግዳወርቅ ታደሰ የተባሉት አስተያየት ሰጪ እንዳሉት በሚኒስቴሩ የሚነሱትን የውስጥና የውጭ ቅሬታዎች ምንጮችን በጥናት የመለየትና ወቅቱ የሚጠይቀውን የማሻሻያ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ይህም የመስሪያ ቤቱን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል። አቶ አብርሃም ምናሉ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በሚኒስቴሩ የሚተገበሩትን የለውጥ መሳሪያዎች አስፈላጊነት በተመለከተ ግንዛቤ መፍጠርን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን የሟሟላት ተግባራት መከናወን እንዳለባቸወ ገልፀዋል። ወደ ሚኒስቴሩ የሚመጡ አዳዲስ አመራሮች እየተገበሩት ያለውን የለውጥ ተግባራት ለመደገፍ ሁሉም ሰራተኛ በንቃት መሳተፍ  ይገባዋል ሲሉ አስተያየት የሰጡት ደግሞ ወይዘሮ ፀጋ ተካ የተባሉ ሰራተኛ ናቸው። ዘንድሮ የሚከበረው የፐብሊክ ሰርቪስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ17 ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ12 ጊዜ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም