የሰራዊቱ ድጋፍ ችግራቸውን እንደፈታላቸው የክምር ድንጋይ ነዋሪዎች ገለፁ

207

ባህርዳር የካቲት10/2012. የምዕራብ እዝ የመከላከያ ሰራዊት የገነባው ደረጃውን የጠበቀ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረባቸውን ችግር እንደፈታላቸው የክምር ድንጋይ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በክምር ድንጋይ የትምህርት ቤቶች ጉድኝት ሱፐር ቫይዘር መምህር ተመስገን መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት የምዕራብ እዝ የሰራዊት አባላት ያስገነቡት ትምህርት ቤት የአካባቢውን ችግር የሚፈታ ነው።

በጉና በጌምድር ወረዳ ከሚገኙ 46 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚመጡ ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ  የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሁለት ብቻ በመሆናቸው ተጨማሪ ትምህርት ቤት የህዝቡ ቁልፍ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።

በተለይም 40ዎቹ ትምህርት ቤቶች የሚገኙት በክምር ድንጋይ ከተማ ዙሪያ በመሆኑ የሚጠቀሙት የክምር ድንጋይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በመሆኑ 80 ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲማሩ ተገደዋል።

በሰራዊቱ የተገነባው ትምህርት ቤት ለዘመናት የዘለቀውን የህብረተሰብ ጥያቄ ከመፍታት ባሻገር 50 ተማሪዎችን በአንድ ክፍል በማስተማር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል ።

ሌላው የክምር ድንጋይ ከተማ ነዋሪ መሪጌታ ማሪ አያናው እንዳሉት በከተማችን ያለው ብቸኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የክፍል ጥበት አጋጠመ እየተባለ በየዓመቱ ገንዘብ እያዋጣን የቆርቆሮ ክፍል ለመስራት እንገደድ ነበር ብለዋል ።

ይህም ልጆቻችን በቅዝቃዜ፣ በአቧራና ነፋስ ለጤና ችግር እየተጋለጡ ነበር ያሉት መርጌታ ማሪ በመከላከያ ሰራዊቱ የተገነባው ትምህርት ቤት የልጆቻቸውን ችግር የፈታ መሆኑን ተናግረዋል።

እርሳቸውም እንደ ሃይማኖት አባትነታቸው ማህበረሰቡን በማስተባበር በትምህርት ቤቱ ውስጥ ችግኝ በመትከል፣ አጥር በማሳጠርና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚሰሩ ገልፀዋል ።

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ብላታ አቸነፍ እሸቴ በበኩላቸው ከተማዋ ከደብረታቦር በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ በመሆኑ የወረዳነትና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጥያቄን ለማስመለስ ከፍተኛ ትግል በማድረግ ማሳካት መቻላቸውን አውስተዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በከተማው ያለው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የክፍል ጥበት በማጋጠሙ ህብረተሰቡ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ ጊዜያዊ ክፍሎችን በቆርቆሮ ቢገነባም ችግሩን መቅረፍ አልቻለም ነበር ብለዋል ።

አሁን የመከላከያ ሰራዊቱ በታሪካዊው የጉና ምድር ትምህርት ቤቱን አስገንብቶ ለህዝብ ማስረከቡ የነበረብንን ችግር ከመቅረፍ ባሻገር ለህዝብ ያለውን ፍቅር ያሳየበት በመሆኑ በሰራዊቱ ከርተናል ሲሉ ተናግረዋል ።

የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ዳምጤ እንዳሉት ደግሞ ዛሬ በዓለም አገራት መካከል የሚታየው የሃብት ልዩነት ካላቸው የሳይንስን ቴክኖሎጂ እውቀት የመነጨ ነው ።

የእድገት ምንጩ ቀድሞ የገባቸው አገራት ህጻናትና ታደጊዎችን በማስተማር በእውቀትና ክህሎት የበለጸጉ በማድረጋቸው መሆኑን ጠቁመው ይህን የተረዳው የአገራችን መንግስትም ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ  ነው ብለዋል ።

የመከላከያ ሰራዊቱ ትምህርት ቤቱን ገንብቶ ማስረከቡም የመንግስትን የልማት ክፍተት የሚሞላ መሆኑን ጠቁመው አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ፈጥኖ ስራ እንዲጀምር ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል ።

የጉና በጌምድር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 40 ክፍሎችን የያዙ ስምንት ህንጻዎች ያሉት ሲሆን ከ22 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት መሆኑ ታውቋል።

በጉና በጌምድር ወረዳ ከ6 ሺህ 400 በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ከወረዳው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።