በድሬዳዋ የጅብ መንጋን ለማባረር በቅንጅት እየተሰራ ነው

144
ድሬዳዋ፣ የካቲት 10/2012 (ኢዜአ) ድሬዳዋ ከተማ ገንደ ሮቃ በተባለው ስፍራ የሚርመሰመሰው የጅብ መንጋ ከአካባቢው ለማባረር የተቀናጀ ስራ እየተካሔደ መሆኑን ባለድርሻ አካላትና የአካባቢው ወጣቶች ገለፁ። ከሁለት ሳምንት በፊት አንድ የሶስት ዓመት ህፃን አንጠልጥሎ የወሰደው የጅብ መንጋ የሚኖርበትንና በብዛት የሚንቀሳቀስበትን አካባቢ በድሬዳዋና በፌደራል መንግስት ተቋማት ቅንጅት በማሽነሪና በሰው ሃይል እንዲፀዳ እየተደረገ መሆኑን የሚመለከታቸው አካላት ተናግረዋል። ገንደ ሮቃ የተባለው ሰፈር የሚገኝበት የቀበሌ 03 መስተዳድር ስራ አስፈጻሚ አቶ ቢንያም ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት ጅቦቹ የሚደበቁበትን ጥሻዎች በጥናት በመለየት እንዲፀዱና ጅቦቹ አካባቢውን ለቀው እንዲሔዱ እየተደረገ ነው። በተለይ በተለምዶ ሰባተኛ በሚባለው አየር ኃይል ጊቢ የጅቦች መኖሪያና መደበቂያ የነበሩትን ስፍራዎች  በዘመቻ እንዲፀዱ ተደርጓል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል የምስራቅ አየር ኃይል ምድብ ተወካይ ሻምበል መጎስ መኮንን በበኩላቸው ጅቦቹ በቀን በአየር ሃይል ጊቢ ውስጥ በመዘዋወር በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሲያደርሱ መቆየታቸውን ገልፀዋል። ‹‹በአንድ የሠራዊት አባል ቤት ድረስ ዘልቆ በመግባት ትንቅንቅ ገጥመው አባላችንንና በሌላ የሶስት ዓመት ህፃን ላይ ጉዳት አድርሶ ነበር›› ብለዋል፡፡ አሁን የተጀመረውን ስራ በማጠናከር ጅቦቹን ከአካባቢው የማስወጣት የተቀናጀ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሻምበል ሞጎስ ተናግረዋል። የጅብ መንጋው  ዋና መሰባሰቢያ  ስፍራ እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ድርጅት የድሬዳዋ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልአዚዝ መሀመድ ጅቦቹ ሌላ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርሱ ጎሬዎቹን የማጥፋት ስራ መከናወኑን ገልፀዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን የደን ጥበቃና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ሁሴን አብዱረህማን እንዳሉት ጅቦች በአካባቢው በከፍተኛ ደረጃ መራባቸውን ተከትሎ በነዋሪዎችና በተቋማት ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በሰው መኖሪያ ስፍራ ጅቦች ሊኖሩ አይገባም ያሉት ቡድን መሪው ጅቦች በሰላም አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ካልሆነ ግን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲገደሉ ይደረጋል ብለዋል። ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በሚከናወኑ ስራዎች ፖሊስ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከዚራ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ትዕግስት ተሾመ ናቸው፡፡ የዛሬ ሁለት ሣምንት የጅብ መንጋ ህፃኑን አንቆ ሲጓዝ የድረሱልን ኡኡታ ያሰሙት ወይዘሮ ትዕግስት ጌታቸው በበኩላቸው ከዚያ በፊትም በሶስት ህፃናትና በፍየሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል። ወጣት ናትናኤል ዮሃንስ እንደገለፀው ደግሞ የአካባቢው ወጣቶች ከ03 ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የጅቦቹ ምቹ መደበቂያ የነበረውን ጎሬ ማጽዳታቸውን ተናግሯል፡፡ ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እስኪሰጠው ድረስም ሶሰት ጅቦች በወጥመድና በተለያዩ መንገዶች መገደላቸውን ወጣቱ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም