በአማራ ክልል የስነ-ምግባር ግድፈት ያሳዩ 65 ሰራተኞች ህጋዊ አርምጃ ተወሰደባቸው

248

ባህር ዳር ኢዜአ የካቲት10/2012 በአማራ ክልል በጥቅም ትስስር የቀን ገቢ ጥናትን በመሰረዝ ፣ ዝቅ አድርጎ በመገመትና ተያያዥ የስነ ምግባር ጉድለት በተገኘባቸው 65 የጉምሩክና ገቢዎች ሰራተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለፀ ።
የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን በባህርዳር ከተማ እየተካሔደ ባለው የቢሮው የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ ላይ እንደ ተናገሩት የክልሉ የገቢ አቅም እንዳያድግ እንቅፋት የሆኑ ሰራተኞችን በጥናት በመለየት የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል።

በሰራተኞቹ ላይ እርምጃው የተወሰደው የተጣለባቸውን ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከግብር ከፋይ ነጋዴዎች ጋር ያልተገባ ግንኙነት በመፍጠር ለግል ጥቅማቸው ሲሰሩ በተጨባጭ በመገኘታቸው እርምጃው እንዲወሰድ ሆኖአል።

ይህ ህገ ወጥ ድርጊትም የክልሉን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከመጉዳቱም ባለፈ ሌሎች ታማኝና የህዝብን አደራ ከዳር ለማድረስ ቀን ከሌሊት የሚታትሩ ምስጉን ባለሙያዎች ስም ጭምር የሚያበላሽ በመሆኑ እንዲስተካከል ተደርጓል።

እርምጃ ከተወሰደባቸው 65 የገቢ ሰራተኞች መካከል ከባድ ጥፋት ፈፅመው የተገኙ ስድስት ሰራተኞች ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጉን ወይዘሮ ብዙአየሁ አብራርተዋል።

24 ሰራተኞች የአራት ወር ደመወዝ ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ከደረጃ ዝቅ የማድረግ፣ የፅሁፍና የቃል ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ተደርጓል ።

ሰራተኞቹ ከፈፀሙዋቸው ጥፋቶች መካከል የቀን ገቢ ጥናትን በመሰረዝና ዝቅ በማድረግ፣ አለአግባብ ከእዳ ነፃ ነው የሚል ማስረጃ በመስጠት፣ የቀን ገቢ ጥናትን መሰረት አድርገው አለመስራት የመሳሰሉት ይገኙበታል ።

ህጋዊ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ኃላፊዋ ሰራተኛው በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ እራሱንና ቤተሰቡን አደጋ ላይ ከመጣሉ በፊት ህዝብና መንግስት የጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ  እንደሚገባም አሳስበዋል።

በየደረጃው ያሉት የገቢዎች ሰራተኞች  ህገ-ወጥ ነጋዴውን ህጋዊ እንዲሆን ማድረግ ሲገባቸው የወንጀል ተባባሪ ሆኖ መገኘት ህሊናን እንደ መሸጥ ይቆጠራል ያሉት ደግሞ የቢሮው የዕቅድ ፣ ዝግጅትና ክትትል የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አትንኩት በላይ ናቸው።

ህገ-ወጥ ነጋዴውን ለመከታተል እንደሚሰራ ሁሉ ምስጉን ሰራተኞችን ከማበረታታት ባለፈም የስነ ምግባር ጉድለት የሚያሳዩ ሰራተኞችን እየተከታተሉ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው ብለዋል ።

በበጀት አመቱ 14 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በግማሽ አመቱ 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለ በግምገማ መድረኩ ላይ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል።

ዛሬ በተጀመረው የእቅድ  አፈፃፀም ግምገማ የከተማ አስተዳደሮች፣ የዞን እና የወረዳ ገቢዎች መምሪያ እና ጽህፈት ቤቶች አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሲሆኑ በነገው እለትም የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ እውቅና በመስጠት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።