ኢትዮጵያና አሜሪካ በኢኮኖሚ መስክ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ነው

1542

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2012 (ኢዜአ)ኢትዮጵያና አሜሪካ የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ የአገራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ገለጹ።

የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የአሜሪካውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከኢፌዲሪ አቻቸው ገዱ አንዳርጋቸው ጋርም ተወያይተዋል።

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ጋር በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽና በቀጠናው የሰላም ሁኔታ ላይ መክረዋል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ እንደምትደግፍና አገራቱ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ለማጠናከር ተስማምተዋል።

ከዚህ አንጻር ሁለቱ አገራት የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነታቸን አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ የጋራ መግባባት ፈጥረዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ላበረከተችው አሰተዋጽኦ  ማይክ ፖምፒዮ አመስግነዋል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍም አጠናክራ እንደምትቀጥል ፖምፒዮ መግለጻቸውን የኢፌዲሪ የውጭ ገዳይ ሚኒስትር ዴታ አቶ ሬድዋን ሁሴን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ማይክ ፖምፒዮ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር  በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድረገዋል።

በውይይታቸውም አሁን በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ አሜሪካ በምን መልኩ ድጋፍ ማድረግ እንደምትችል ትኩረት አድርገው መክረዋል።

በተለይም አሜሪካ በኢትዮጵያ ከምታደርገው የሰብዓዊ እርዳታ በተጨማሪ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማጠናከርም በሚያስችል ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል።

የአሜሪካ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታና አሜሪካ ለአፍሪካ ከመደበችው ገንዘብ ተጠቃሚ እንዴት መሆን እንዳለባትም ምክክር አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን ለምታደርገው ጥረት አሜሪካ  ድጋፏን ታጠናክራለች ብለዋል።

የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚካሄደው ውይይት አንዳንድ የቴክኒክ፣ የዲፕሎማሲያና የሕግ ጉደዮች እንደሚቀሩትም በምክክሩ ወቅት ተነስቷል።

በመሆኑም ውይይቱ ቀድሞ በተጀመረበት አኳኋን እንዲጠናቀቅ መነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ነበያት ጌታቸው ገልጸዋል።