ለመንግስት ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ሊሰጥ ነው

380

አዳማ (ኢዜአ) የካቲት 09/2012፡- ከመጪው ሚያዝያ ጀምሮ በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ለሚገኙ ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሚሰጥ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የሲቪል ሰርቪስ ብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ፕሮጀክት መጀመረን አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ ፈይሳ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የብቃት ማረጋገጫ ፈተናው የሚሰጠው ከሀገራዊ ለውጡ ጋር የተቃኘ የመንግስት ሰራተኛ እንዲኖርና የወቅቱን የህዝቡ አገልግሎተ  ጥያቄ የሚመልስ ኃይል ለመፍጠር የሚያስችል  ነው።

በአሁኑ ወቅት የህብረሰተቡን የአገልግሎት ፍላጎት ማርካት እንዳልተቻለ ጠቅሰው ለዚህ ምላሽ እንዲሆንም በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ያለው ማንኛውም ሠራተኛ በዚህ የብቃት ማረጋገጫ ውስጥ እንደሚያልፍ  ተናግረዋል።

"የብቃት ማረጋጫው ፕሮጄክቱ ለሁለት ዓመት ተኩል የሚቆይ ነው "ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ከመጪው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ወደ ተቋማቱ አዲስ የሚቀላቀሉ ሠራተኞችም ጭምር የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

በሀገሪቱ ከአንድ ሚሊዮን 700ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች እንደሚኖሩ ያመለከቱት አቶ ብርሃኑ፤ ፕሮጀክቱ በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበትና በመንግስት ተቀባይነት ማግኘቱንና እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ መሆኑን አስረድተዋል።

በኮሚሽኑ የብቃት ማረጋገጫ ፕሮጄክት ሥራ አስኪያጅ አቶ የማነ ኃይሉ በበኩላቸው" የፕሮጄክቱ  ዓላማ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ ለማድረግና የህዝቡን የተገልጋይነት እርካታ ለማረጋገጥ ነው "ብለዋል።

ሀገሪቱ የቆየና ዘመን ተሻጋሪ መንግስታዊ የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት ቢኖራትም በተለይም ከአቅም፣ አመለካከት፣ አስተሳሰብና ተግባቦት አንጻር ሰፊ ክፍተት እንዳሉ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የተቀረጸው  ሀገሪቱ የደረሰችበትን ደረጃ የሚመጥንና ከለውጡ ጋር የታቀኘ አስተሳሰብና ተግባር ያነገበ  እውቀት፣ ክህሎትና በአመለካከት የበቃ የሰው ኃይል በአዲስ መልክ ማደረጀት በማስፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

የብቃት ማረጋገጫ ፈተናው የየሴክተሮቹን ዓላማ መሰረት ባደረገ መልኩ በሠራተኞች እውቀትና ክህሎት ላይ በመመስረት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሥር ሆኖ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረኩ ከፌዴራል፣ ከክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም