የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞት ለመቀነስ በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት ጉልህ ሚና አላቸው

87

አዲስ አበባ የካቲት 9/2012 (ኢዜአ) የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ ተገለጸ። ይህ የተነገረው  አዲስ አበባ ውስጥ በተካሔደው የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሃኪሞች ማህበር 28ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት የስነ ምግብ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም ጉባኤውን ሲከፈት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ መሰረታዊ የጤና አገልገሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ብዙ ሰርታለች።

ከዚህ ውስጥም በወሊድ ወቅት የሚከሰት የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞት ቅነሳ ስራ ተጠቃሽ ነው።

ከዚህ ቀደም ከ100 ሺህ በህይወት ከሚወለዱ ጨቅላ ህጻናት 1 ሺህ 250 ዎቹ በወሊድና ተያያዥ በሆኑ የጤና እክሎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ አስታውሰው፤ አሁን ይህ አሃዝ ወደ 353 ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።

በዚሁ በተከናወኑት ተግባራትም የእናቶችን ሞት በ72 በመቶ የህጻናትን ደግሞ በ62 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

ለዚህ ስኬት ደግሞ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባሻገር በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት ጉልህ ሚና እንደነበራቸው አስረድተዋል።

የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሃኪሞች ማህበር ከጤና ሚኒስቴርና ከጤና ተቋማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከራቸው ለውጥ ለማምጣት ማስቻሉን ዶክተር መሰረት ጠቁመዋል።

ማሕበራቱ በእውቀት ሽግግር፣ ልምድ ልውውጥና ፖሊሲ ቀረጻ ከሚኒስቴሩ ጋራ በቅንጅት እየሰራ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሃኪሞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር እድልአየሁ በቀለ የሙያ ማህበሩ የተቋቋመው ደረጃውን የጠበቀ የስነ ተዋልዶ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

''በመሆኑም አባላቱ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በስነ ተዋልዶ ዙሪያ በትኩረት እየሰሩ ነው'' ብለዋል።

በዋናነትም የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞት ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በማህበሩ አባላት የሚሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የሙያተኛውን አቅም እያጎለበቱ መሆኑን አንስተዋል።

ዘመናዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ፣ የግብአትና የፋይናንስ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል ማህበሩ ከሚኒስቴሩ ጋር በመተባበር  እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

በጉባኤ ላይ ከኤርትራ የተጋበዙ የማህጸንና ጽንስ ሃከኪሞች እየተሳተፉ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ በመድረኩ የስነ ተዋልዶና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽነትና የእናቶችና የህጻናት ጤና አጠባበቅን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሃኪሞች ማህበር ከተመሰረተ 28 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ከ500 በላይ አባላት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም