ፌስቲቫሎች ከከተማ ውጭ የገጠር አርሶ አደሮችንም ማዝናናት አለባቸው

62

አዲስ አበባ፣የካቲት 9/2012 (ኢዜአ) ፌስቲቫሎች ከከተማ ውጭ አርሶ አደሮችንም ማዝናናት አለባቸው ተባለ።

በአገር አቀፍ ደረጃ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የአርሶ አደሮች ፌስቲቫል በበቆጂ ከተማ ትናንት ተካሂዷል። በምስራቅ አርሲ ዞን የበቆጂ ከተማ ዙሪያ አርሶ አደሮችን ያሰባሰበው ፌስቲቫል የተለያዩ የመዝናኛ ክንውኖችን ባካተተ መልኩ ተከውኗል።

በፌስቲቫሉ ፈረስ ጉግስ፣ ሩጫ፣ የገንፎ አመጋግብ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን አርሶ አደሮች ሞፈርና ቀንበራቸውን ጨምሮ የእርሻ ምርትና ሌሎች መገልገያ መሳሪያቸውን ያሳዩበት ኤግዚቪሽን ተካሂዷል።

ፌስቲቫሉን ያዘጋጀው የአካባቢው ተወላጅና የጭላሎ ሚዲያ ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ አንዷለም ጌታቸው ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመተባበር ነው።

አዘጋጁ እንደሚገልጸው፤ ፌስቲቫሉ የካቲት ወር አርሶ አደሩ ምርቱን ሰብስቦ እረፍት የሚያደርግበትና ለቀጣይ የምርት ዘመን የሚዘጋጅበት በመሆኑ አርሶ አደሮችን ለማነቃቃት በማለም ነው።

''ከ80 በመቶ የማያንሰው ህዝብ አርሶ አደር በሆነባት ኢትዮጵያ ግብርናው ትልቅ ተስፋ ነው'' ያለው ጋዜጠኛ አንዷለም፤ ለአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ፌስቲቫል ለሌሎች አካባቢዎች ትምህርት እንደሚሆን ጠቁሟል።

በፌስቲቫሉ ላይ የታደሙት የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር ፌስቲቫሉ በአርሶ አደሮች መካከል ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በአርሶ አደሮች መካከል ከሚፈጠረው የልምድ መለዋወጥና መዝናናት ፋይዳው በተጨማሪ ለአርሶ አደሮች ቴክኖሎጂ አጠቃቅም ለግብርናው ዕድገት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

ይህን የአርሶ አደሮች ፌስቲባል ከባዛርና ኤግዚቢሽኖች በተጨማሪ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ ለማዘጋጀት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው ማድረግ ያለበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠው፤ ግብርና ሚኒስቴር ፌስቲቫሉን ምርትን ለማሳደግ በሚያስችል መንገድ ሊያስፋፋው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም