የቦቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አትሌቶች የውሃ እጥረት እየፈተናቸው ነው

98

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9/2012 (ኢዜአ) የአትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው ቦቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ውስጥ የሚሰለጥኑ አትሌቶች የውሃ እጥረት ፈተና ሆኖባቸዋል።

የመጀመሪዋ አፍሪካዊት የኦሎምፒክ 10 ሺህ ሜትር ባለድሏ አትሌት ዋና ሱፐር-ኢንተንደንት ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ዓለምን ያስደመሙና ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያኮሩ ሯጮች መፍለቂያ ናት በቆጂ።

በርካታ አትሌቶችን ባፈራቺው የቦቆጂ ከተማ በ2004 ዓ.ም በደራርቱ ቤተሰቦች የተንጣለለ ማሳ ላይ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ተቋቁሟል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ እስካሁን 223 አትሌቶችን ተቀብሏል።

ዓላማውም ሰልጣኞችን አዘጋጅቶ ለአገር ውስጥ ክለቦች መስጠት ሲሆን፣ የዘንድሮውን ሳይጨምር 122 ሰልጣኞች ወደ ክለቦች ተዘዋውረዋል።

በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ የዞን ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባወጣው መመዘኛ መስፈርት የሚመለመሉት አትሌቶች እንደ ዝላይ፣ ውርወራና መሰል የሜዳ ተግባራት ስልጠና ይሰጧቸዋል።

”የቦቆጂና ሩጫ ትስስር አሁንም ተስፋ ያለው ነው” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ የተቀዛቀዘውን ስሜት ለማነሳሳት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰልጣኞቹ የመኝታ፣ የምግብ፣ መደበኛ ትምህርትና ሌሎች አገልግሎት ያገኛሉ።

ዳሩ ግን ማዕከሉ የውሃ ዕጦት ፈተና እንደሆነበት አቶ ሃይሉ ያመለክታሉ።

ማዕከሉ የውሃ አገልግሎት ስላልተገነባለት የመጠጥ ውሃን ጨምሮ ለሁለት አትሌቶች በቀን አንድ ጄሪካን ውሃ በግዥ ለማቅረብ መገደዱን ገልጸዋል።

ዘንድሮ ለተቀበላቸው 20 ወንድና ሴት ሰልጣኞች በቀን 20 ጀሪካን ውሃ ቢገዛ እንኳን፤ ፍላጎታቸው እንዳልተሟላ ይናገራሉ።

ሰውነታቸውን ለመታጠብ የሻወር አገልግሎት ለማግኘትም ከማዕከሉ ውጭ ለመሄድ መገደዳቸውን አመልክተዋል።

እንደ አማራጭም ማዕከሉ በአካባቢው ከሚገኘው የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከማዕከሉ ሰልጥነው የወጡ አትሌቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ መሆናቸውን አቶ ኃይሉ ገልጸዋል።