የቆላ ስንዴ ልማት ፕሮጀክት ክልሎች በባለቤትነት እንዲመሩት ተጠየቀ

286

ሰመራ፣ የካቲት 8/2012 (ኢዜአ) በስንዴ ልማት መስክ የተጀመረዉ ስራ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ክልሎች ስራውን በባለቤትነት መምራት እንደሚገባቸው የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።

በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ በግብርና ምርምር ማእከል እየተካሔደ የሚገኘውን የዘር ብዜት ማእከልና በአይሳኢታ ወረዳ በከፊል አርበቶ አደሮች የሚለማውን የቆላ ስንዴ ልማት ዛሬ በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር አቶ ኡመር ሁሴን እንደተናገሩት ሀገራችን የስንዴ ፋላጎቷን በመጪዎቹ 3 አመታት በራሷ አቅም ለመሸፈን ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ መስኖ ልማት ተገብቷል።

በዚህ አመትም በአዋሽ፣ ኦሞና ሸበሌ ተፋሰሶች  ከ15 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ስንዴ በመስኖ እየለማ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 12 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በአዋሽ ተፈሰስ ውስጥ የሚለማ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሳን ለመቻልና ሀገራዊ የግብርና ዘርፉ ትራንስፎርሜሸን ለማረጋገጥ የቆላማ አካባቢዎቸን በመስኖ ማልማት ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንደሚገባው አመላካች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

የተጀመረው የቆላ ስንዴ ልማትም ሆነ ተያያዥ ገበያ ተኮር የግብርና ስራዎች ውጤታማ ሆነው በዘርፉ ራስን ከመቻል ባሻገር ወደ ኤክስፖርት ለመሸጋገር የተጀመረውን የቆላ ስንዴ ልማት ክልሎች በባለቤትነት ስራውን ይዘው መምራትና መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝን ተጠቅሞ በአመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ማምረት የሚቻልበት ሰፊ እድል መኖሩን ተናግረዋል።

ይሁንና የህብረተሰቡ የአመለካከት ችግርና የስራ ባህል ዝቅተኛ መሆን አብዛኛውን ከፊል አርብቶ አደር ከአንድ ጊዜ በላይ ማምረት እንዳልቻለ ገልፀዋል።

አሁን የተጀመረው የስንዴ ልማት ህብረተሰቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ህይወቱን የሚያሻሽል ብቻም ሳይሆን ከፊል አርብቶ አደሩ  በአመት ሁለት ሶስት ጊዜ እንዲያለማ የማላመድ መልካም አጋጣሚ መፈጠሩን አስረድተዋል።

የክልሉ መንግሰትም በዘርፉ ለሚሰማሩ ወጣቶችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግብርና ስራቸው የሚያስፈልጉ የማሽነሪ ፣  የግብርና ግብአት ፣ የገበያ ትስስርና የብድር አቅርቦት ለማመቻቸት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የክልሉ አርብቶ አደር ፤እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃፊ አቶ አሊ ሁሴን በበኩላቸው በክልሉ በመጪው አመት ከ1 ሺህ 400 በላይ የተማሩ ወጣቶችን በስንዴና ተያያዥ የግብርና ልማት መስክ ለማሳተፍ እቅድ ተይዞ እተሰራ ነው።

ለዚህም በተለያዩ የግብርናና ቢዝነስ መስኮችን ጨምሮ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በዲፕሎማና በዲግሪ የተመረቁ ልጆች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።

በአይሳኢታ ወረዳ በሳህሌ ቀበሌ ስንዴ በማህበር እያለሙ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል  ወጣት ሃቢብ መሃመድ እንደተናገረው ስንዴ ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው ሊለማ ይችላል የሚል አስተሳሰብ እንዳልነበራቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢስቲትዪት ባደረገላቸው የግብአትና የሙያ ድጋፍ በአሁኑ ሰአት ከ90 በላይ ሰዎችን በማበብር ተደራጅተው 200 ሄክታር መሬት እያለሙ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናትና ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድርና የሱማሌና አማራ ክልል ተወካዮች ተሳትፈዋል።