ወላይታ ድቻ ባህር ዳር ከነማን 1 ለ ዜሮ አሸነፈ

81
ሶዶ የካቲት 08/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ወላይታ ዲቻ ተጋጣሚውን ባህር ዳር ከነማን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸነፈ። ዛሬ በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲዮም በተካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ተጋጣሚውን ባህር ዳር ከነማን 1 ለ ዜሮ በሆነ ውጤት አሸንፎ ወጥቷል። ወላይታ ድቻ አሸናፊ ያደረገውን ግብ ያስቆጠረው በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው የባከነ ደቂቃ 10 ቁጥሩ ባዬ ገዛኸኝ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ አማካኝነት ነው። መጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኳስ በማደራጀት በመከላከል  በማጥቃት በሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል በመድረስና ዕድል በመፍጠር ረገድ ወላይታ ድቻ የተሻለ ነበር። ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ከነበረው የመሸናነፍ ስሜት የተነሳ ውጥረት የተሞላበት እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን የሜዳውን እንቅስቃሴ በመቆጣጠርና አስደንጋጭ የግብ ሙከራዎች በማድረግ ወላይታ ድቻ የተሻለ ሆኖ አምሽቷል። በዚህም ወላይታ ድቻ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባስቆጠራት ግብ ታግዞ ተጋጣሚውን በማሸነፍ ነጥቡንም ወደ 21 ከፍ ማድረግ ችሏል። በሌላ በኩል በትግራይ ዓለም አቀፍ ስታድዮም ዛሬ ጨዋታቸውን ያደረጉ ስሁል ሽረ እና ሀዲያ ሆሳዕና ሳይሸናነፉ በአቻ ውጤት ተለያዩ። በዛሬው ጨዋታ  ሀድያ ሆሳእና ከስሁል ሽረ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያሳይም ያለ ምንም ግብ  ነጥብ ተጋርተው ተለያይተዋል። ስሁል ሽረዎች በአንፃሩ አልፎ አልፎ  ያገኙዋቸውን ጥሩ  አጋጣሚዎች ሳይጠቀምባቸው በመቅረት  በደጋፊው ፊት ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት ተገዷል። የሀድያ ሆሳእና አሰልጣኝ ጸጋይ ኪዳነማሪያም እንዳሉት  ግብ ባናስቆጥርም ጥሩ በመጫወታችን  ተደስቻለሁ ብለዋል። የስሁል ሽረ አሰልጣኝ ሳምሶም አየለ በበኩላቸው እንደበፊቱ ባለመጫወታችን በደጋፊያችን ፊት ነጥብ ተጋርተን ለመውጣት ተገድደናል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም