ጥናትና ምርምር የሚደረግበት የሰው ሃይል ማበልጸጊያ የልህቀት ማዕከል ሊገነባ ነው

2051

አዲስ አበባ  ሰኔ 20/2010 ከፍተኛ ቴክኖሎጂን ለሚጠይቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች  የሰው ሃይል ማበልጸጊያ የልህቀት ማዕከል ሊገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታየውን ተግዳሮት ለመፍታትና ወጭ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ የጥናትና ምርምር ስራ እያካሄደ መሆኑንም ገልጿል።

በኮንስትራክሽን ዘርፉ የተሰማሩ ስራ ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና አስፈጻሚ አካላት በተገኙበት ሶስተኛው አገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር አውደ ጥናት ተጀምሯል።

በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ እንደተናገሩት ” የኮንስትራክሽን ዘርፉ  ፈጣን እድገት በማረጋገጥ የበለጸገች አገር ለመገንባት በሚሰራው ስራ ውስጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል።”

መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ለውጥና እድገት እንዳልተገኘበት ጠቅሰዋል።

የኮንስትራክሽን ዘርፉን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አለመምራትና ደካማ  የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት መኖር ዘርፉ ዘመናዊ አሰራርን እንዳይከተል አድርጎታል ብለዋል።

በተመሳሳይ የሙያ ብቃቱ የተረጋገጠ ባለሙያ እጥረትና ኋላ ቀር የግንባታ ዘዴዎችና የግብዓት አቅርቦት ችግሮችም የዘርፉ ሌሎች ተግዳሮቶች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

በመሆኑም ለዘርፉ ዋነኛው ተግዳሮት የባለሙያ እጥረት በመሆኑ ከፍተኛ ቴክኖሎጂን ለሚጠይቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጥናትና ምርምር የሚያከናውኑ የሰው ሃይል ማበልጸጊያ የልህቀት ማዕከል ሊገነባ መታቀዱን ገልጸዋል።

የልህቀት ማዕከሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚካሄዱበት ሲሆን የፕሮጀክቶችን የጥራት ጉድለት እና በተያዘላቸው ጊዜና በጀት አለመጠናቀቅ ችግርን የሚፈታ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

ኢንስቱትዩቱም የዘርፉን ተግዳሮት ከግምት በማስገባት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከውጭና አገር ውስጥ የጥናትና ምርምር ተቋማት ጋር የምርምር ስራዎችን በማከናወን  ወጭ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን የመለየት ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ወጭ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በመለየት ለኢንዱስትሪው የማስተዋወቅና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራም እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

እነዚህ ወጭ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች በአዕምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ማረጋገጫ የተሰጣቸው  ሲሆን፤ እየተካሄደ በሚገኘው በሶስተኛው አገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር አውደ ጥናት ላይም ውይይት ተደርጎባቸው ወደ ተግባር እንዲገቡ ይደረጋልም ነው ያሉት።

እንዲሁም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት የእውቀት መስኮችን ሊያዘምኑ የሚችሉ 18 ማኑዋሎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ በቅርቡ ለኢንዱስትሪው የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል ብለዋል።

ይህም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ዘርፍን በዘመናዊ መንገድ እንዲመራ ከማድረግ ባለፈ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ፣  የእውቀት ሽግግር እንዲኖርና የጥራትና የባለሙያ እጥረትን ለመቅረፍ እንደሚያግዝም ተጠቅሷል።