በአዲስ አበባ ከለቡ-ጀሞ የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት በይፋ ተጀመረ

120

አዲስ አበባ የካቲት 8/2012(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ከለቡ ጀሞ የተሰራውን የሞተር አልባ ትራንፖርት አገልግሎት መስጫ መንገድ አስመርቆ ሥራ አስጀምሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ስጦታው አካለ እንዳሉት የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩ ነዋሪው ብስክሌትን እንደ አንድ የትራንስፖርት አማራጭ እንዲጠቀም ታስቦ ነው።

የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት፤ በሰዎች የአካል እንቅስቃሴ ማነስ ምክንያት ለሚመጣ የጤና ችግር፣ ወጪ ለመቀነስና የአየር ብክለትን ለመከላከል ጉልህ ፋይዳ አለው።

ለከተማዋ የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን በዓይነትና  በብዛት ተደራሽ ማድረግም ለነገ የሚባል ጉዳይ አለመሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም በቅርቡ ከቃሊቲ- ቱሉ ዲምቱ 11 ኪሎ ሜትር መንገድ እና ከሃይሌ ጋርመንት- ጅሞ 4 ኪሎ ሜትር መንገድ ተመሳሳይ የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት ይጀመራል ብለዋል።

መንገዱ ለብስክሌት ተጠቃሚዎች ተደራሽ መደረጉ ለጤናማ እንቅስቃሴ፣ የመንገድ መዘጋጋትን ለመቀነስ፣ ለመዝናናት፣ የድምጽና የአየር ብክለትን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የሞተር አልባ ትራንስፖርት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ መንገድ ተጠቃሚዎችን ከአደጋ መታደግ ተቀዳሚ ዓላማው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በከተማዋ "አብነት" እና "ስታዲየም" አካባቢዎች የብስክሌት መለማመጃ ቦታዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቃው ከለቡ-ጀሞ የተሰራው የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ መንገድ የ2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አለው።

በመጪዎቹ 10 ዓመታት የ100 ኪሎ-ሜትር የብስክሌት ትራንስፖርት መስመር ለመዘርጋት መታቀዱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከገርጂ 22 ጤና ጣቢያ እና ሲኤምሲ መንገድ ላይ የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት ተጀምሮ መቋረጡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም