ናይጄሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ አጋርነት ማጠናከር ትሻለች

55
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያና የናይጄሪያን የኢንቨስትመንትና ንግድ አጋርነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የናይጀሪያ አምባሳደር ባንኮሌ አዴዬ ገለጹ። በቅርቡ የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃሙዲ ቡሃሪ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝትም የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያደርሰው ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የናይጄሪያ አምባሳደር ባንኮሌ አዴዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ያላቸው አገራት ናቸው። በተለይም በፖለቲካው መስክ ያላቸው የትብብር አድማስ ሠፋ ያለና ጠንካራ መሆኑን ጠቁመው በምጣኔ ኃብት ረገድም እያደገ የመጣ ግንኙነት አላቸው ብለዋል። የናይጄሪያ ባለኃብቶች በምግብና መጠጥ ኢንደስትሪው መሳተፋቸውን የጠቆሙት አምባሳደሩ የዳንጎቴ ግሩፕም በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ፋብሪካ ከፍቷል ብለዋል። ያም ሆኖ የምጣኔ ኃብት አጋርነቱ የሚጠበቀውን ያክል ባለመሆኑ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የሁለቱን አገራት ምጣኔ ኃብታዊ ትብብር ለማጠናከር ርብርብ መደረጉን ገልጸዋል። ለዚህም በናይጄሪያ አንድ የሚኒስትሮች የጋራ ምክክር መድርክና አንድ ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎች የምክክር መድረክ መካሄዱንም ነው የጠቆሙት። አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ሦስተኛው የጋራ የሚኒስትሮች ስብሰባ እንደሚካሄድ ገልጸው ይህንንም ተከትሎ የጋራ የንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮች ይፈለጋሉ ነው ያሉት። የኢትዮጵያን ቡናና የማር ምርት በናይጄሪያ የገበያ አድል እንዲያገኝ ትኩረት ይደረጋል ያሉት አምባሳደሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ለዚህ ትልቅ አጋዥ ይሆናል ብለዋል። በቅርቡ የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃሙዲ ቡሃሪ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝትም የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያደርሰው ጠቁመዋል። ናይጄሪያና ኢትዮጵያ የአገራቸው ዲፕሎማትና ባለሥልጣናት ጉዞ የሚያቀልላቸውን አንድ ወጥ የቪዛ  አገልግሎት ለማስጀመር ተስማምተዋልም ብለዋል። አገራቱ ያሉባቸውን የጋራ የጸጥታና የደህንነት ስጋት ለመከላከል የሚያስችል በመከለከያ ዘርፍ ላይ በትብብር መሥራታቸውን አምባሳደሩ ጠቁመዋል። የፕሬዚዳንት ቡሃሪን ጉብኝት ተከትሎ በአገራቱ መካከል የተደረሱ ሥምምነቶችና የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ይበልጥ ይጠናከራሉም ብለዋል። ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ተመሳሳይ የፌዴራሊዝም ሥርዓት የሚከተሉ አገራት በመሆናቸው በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ናይጀሪያ ዝግጁ ነች ብለዋል አምባሳደሩ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም