ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ስፖርቶች ተሳትፎዋን ማሳደግ እንዳለባት ገለጹ

110
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከውስን የስፖርት አይነቶች ወጥታ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ተሳትፎዋን በማሳደግ ውጤታማ እንደምትሆን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ሊካሄድ ከስድስት ወራት ያልበለጠ ጊዜ ይቀረዋል። ለዚህም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ቅድመ ዝግጅት በሥሩ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር እየሰራ ይገኛል። በዛሬው እለትም በሁሉም ክልሎች የሚዞረው የኦሎምፒክ ችቦ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተለኩሷል። በእለቱ የማህበረሰብ የጤና እና የአካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተካሂዷል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች የምትሳተፍባቸውን የስፖርት አይነቶች በማሳደግ መስራት ከቻለች ውጤታማ መሆን ትችላለች ብለዋል። በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ለሚኖራት ተሳትፎ ከዘመቻ ይልቅ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ተይዞ መስራት ይገባልም ነው ያሉት። “ለጥቁር ሕዝቦች ትልቅ የታሪክ ምሳሌ የሆነውን አበበ ቢቂላን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቷ ዛሬም ጠንክሮ ከተሰራ የማይቻል ነገር የለም" ብለዋል። ከታች ጀምሮ በታዳጊ ስፖርተኞች ላይ መስራት እንደሚገባ ገልጸው፣ በተለይ በትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል። "በቶኪዮ ኦሎምፒክ እንደ አገር ውጤት ለማምጣት በሚሰራው ስራ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ከጎናችሁ ነን’’   ሲሉም አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል። ኦሎምፒክ ኮሚቴው ለቶኪዮ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሃብት በማፍራት የኦሎምፒክ መንደር ጭምር ለመገንባት የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል። ዛሬ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የኦሎምፒክ ችቦ የመለኮስ ስነ ስርአት ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች፣ የቀድሞ አትሌቶች እና በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ተገኝተዋል። የኦሎምፒኩ ችቦ ከአዲስ አበባ ዛሬ ድሬዳዋ የተረከበ ሲሆን በቀጣይ ወደ ሁሉም ክልሎች የሚዘዋወር ይሆናል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም