በዋግ ኽምራ የእንስሳት መኖ እጥረት አጋጥሟል

207

ሰቆጣ፣ የካቲት 08/2012(ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በተከሰተው ድርቅ በእንስሳት መኖ እጥረት መቸገራቸውን በእንስሳት እርባታ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

ያጋጠመውን የመኖ እጥረት ለመቅረፍ አርዳታ ሰጪ ድርጅቶችን በማስተባበር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የብሄረሰብ አስተዳደሩ አስታውቋል።

የሰሃላ ወረዳ የጓሮች ቀበሌ ነዋሪ አቶ ማለደ በየነ ለኢዜአ እንደገለፁት በዘንድሮው ክረምት በቂ ዝናብ በአካባቢያቸው ባለመጣሉ መክንያት ድርቅ ተከስቷል።

በእንስሳት እርባታ የሚተዳደሩ በመሆናቸው ባለፉት ስድስት ወራት መኖ ለመፈለግ በረሃ ለበረሃ እየተንከራተቱ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በበረሃው ያለው ቅጠል በጸሃይ በመርገፉና ሳሩም በመመናመኑ ካላቸው 25 ፍየሎች ውስጥ 10ሩን በመሸጥ ለመኖና ለምግብ እህል ግዥ በማዋል ቀሪዎቹን በቤት ለማዋል መወሰናቸውን ተናግረዋል።

በዝቋላ ወረዳ የ04 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቢሰጥ አስረሱ በበኩላቸው አካባቢያቸው ቆላማ በመሆኑ ዋነኛ የመተዳደሪያ ሃብታቸው የሆኑት ፍየሎች በተከሰተው ድርቅ ለመኖ እጥረት ተጋልጠዋል።

በክረምቱ የዘሩትን በቅሎ ምርት ሳይሰጥ በመቅረቱ አገዳውን በመሰብሰብ እስከ አሁን ለመኖ ሲጠቀሙበት ቢቆዩም አሁን በማለቁ ያሉዋቸውን እንስሳት ገበያ አውጥተው ለመሸጥ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የእንስሳት ሃብት ልማት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታደሰ ጥጉየ እንደገለጹት የተከሰተው ድርቅ በማህበረሰቡና በእንስሳቱ ላይ ችግር ፈጥሯል።

የድርቁን ተጽእኖ ለመቀነስም ከ92 ሺህ በላይ በግና ፍየሎች ለገበያ በማውጣት እንዲሸጡ ከማድረግ ባሻገር ከ68 ሺህ በላይ እንስሳት ደግሞ መኖ ፍለጋ ወደ አጎራባች ቀበሌዎችና ወረዳዎች እንዲሰደዱ ግድ ብሏል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም አርዳታ ሰጪ ድርጅቶችን በማስተባበር እስከ አሁን ድረስ 2 ሺህ 500 ኩንታል መኖ መቅረቡንና በዘጠኝ ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተጨማሪ መኖ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መልካሙ ደስታ በበኩላቸው ድርቁ ያስከተለውን ተጽእኖ ለማወቅ በተካሄደ ጥናት ከ106 ሺህ በላይ ህዝብ ለምግብ እህል እጥረት ተጋልጧል።

ይሁን እንጂ በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር 20 ሺህ 721 ኩንታል ስንዴ፣ ክክና ዘይት ቀርቦ ለህዝቡ ተሰራጭቷል።

በመኖ እጥረት ምክንያት በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን ተፅእኖ ለመቀነስ አርሶ አደሩ የእንስሳቱን ቁጥር በመሸጥ እንዲቀንስ ከመስከረም ወር ጀምሮ በተካሄደ ውይይት መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ በሰሃላ እና ዝቋላ ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በሰቆጣ ዙሪያ፣ በደሃና፣ በፃግብጅ፣ በጋዝጊብላ እና በአበርገሌ ወረዳዎች በከፊል ድርቅ መከሰቱ ተመልክቷለል፡፡