ለድሬዳዋ ፍቅር ፣ ሰላምና አንድነት መጠናከር እንሰራለን-- ወጣቶች

69
ድሬዳዋ  የካቲት 8/2012 (ኢዜአ)  ለዘመናት የዘለቀውን የድሬዳዋ ነዋሪዎች ፍቅር ፣ ሰላምና አንድነት የበለጠ እንዲጠናከር እንጂ ወደ ኋላ እንዲመለስ አንፈቅድም ሲሉ የከተማዋ ወጣቶች ገለፁ ። ወጣቶቹ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ሁሉ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል ። የድሬዳዋ ወጣቶች ዳሽን ባንክ በሥራ ፈጠራ ክህሎትና በንግድ አስተዳደር ያዘጋጀውን የአምስት ቀናት ስልጠና ሲያጠናቅቁ እንደተናገሩት የድሬዳዋ መገለጫ የሆነውን ሰላም ፣ፍቅርና አንድነት እንዲደበዝዝ በፍፁም አንፈቅድም ብለዋል ። በሥልጠናው የተሳተፈው ወጣት ያሬድ መኮንን በሰጠው አስተያየት ድሬዳዋ እንደ  ከተማ ከተቆረቆረች ጀምሮ በተሻገረችው አንድ ክፍለ ዘመን ሙሉ ነዋሪዎቿ በፍቅር፣ በአንድነትና በህብረት የሕይወትን ውጣ ውረድ አልፈው የገነቡትን ፍቅር ፣ ሰላምና አንድነት የበለጠ እንዲጠናከር የድርሻችንን ልናበረክት ይገባል ብሏል ። ይህን በመላው ሀገሪቱ መገለጫ የሆናትን ፍቅርና ህብረት ለመናድ የሚደረገውን  የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በፅናት መከላከል እንደሚገባም ወጣቱ ተናግሯል ። ‹‹እኔ የቀሰምኩት እውቀት ወደ ስራ የሚለወጠው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው ያለው ወጣቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ከእኛ ከወጣቶች ብዙ ይጠበቃል የሚል አስተያየት ሰጥቷል ። በከተማው አልፎ አልፎ ሆን ተብሎ የሚከሰተው ረብሻ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ያነገቡት ተልዕኮ በመሆኑ ወጣቱ ተደራጅቶ በመከላከል ለህግ ማቅረብ እንዳለበት የገለፀው ደግሞ የከተማዋ ወጣት አብዱልሃኪም አህመድ ነው፡፡ እኔ ባለሁበት ቀበሌ ኃላፊነቴን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ያለው ወጣቱ መንግስትም ለስራ አጥ ወጣቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሥራ ዕድል ማመቻቸት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ተመሣሣይ ሃሳብን ያንፀባረቀው ወጣት ኤርሚያስ ተፈራ በበኩሉ በጎሳ ፣በብሔርና በኃይማኖት ሽፋን ሀገር እንዲተራመስ ሥራ እጥነት የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ በመሆኑ የድሬዳዋ አስተዳደር ስራ አጥነትን ለማቃለል ከቃል የዘለለ ተጨባጭ ሥራ መስራት እንዳለበት ገልጿል፡፡ ወጣት አሊ ሁሴን እንደ ገለፀው ደግሞ መንግስት የራሱን አመራሮች በተገቢው መንገድ በየጊዜው መገምገምና እርምጃ መውሰድ ከቻለ በከተማዋ እየተስተዋለ የሚገኘው የሰላም መደፍረስ መቆጣጠር ይቻላል ። በከተማና በገጠር የምንገኝ ወጣቶች በየጊዜው ስለ ድሬዳዋ ህብረትና  አንድነት እየተወያየን የቆየውን በሰላምና በፍቅር የተገነባውን ማንነታችን ለማደብዘዝ የሚሰሩ አጥፊዎችንና ሁከት ፈጣሪዎችን ለህግ በማቅረብ ኃላፊነታችን ለመወጣት ቃል ገብተናል ብሏል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር የሥራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ባዬ እንደገለፁት ወጣቱ ለሚጠይቃቸው የማምረቻና የመሸጫ ሥፍራዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በርካታ ግንባታዎች መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡ ወጣቱ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ የጀመረው ተግባር በማጠናከር የልማት ተሳታፊነቱንና ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ አስተዳደሩ ተገቢውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም