የወረታ ወደብ የውጭ ንግድ ትስስርን ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድገዋል

91

አዲስ አበባ የካቲት 7/2012 "የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ግንባታ የክልሉን ቀጠናዊ የውጭ ንግድ ትስስርን ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድገዋል "ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

በመጀመሪያው ምዕራፍ በ3 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባውና  በአንድ ጊዜ 973 ኮንቴነሮችን  ማስተናገድ የሚችለው የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ዛሬ ተመርቋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በምረቃው ወቅት እንደገለጹት  የወደቡ ግንባታ የክልሉን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት  ለማጎልበት ያግዛል።

በተለይም ከጂቡቲ ወደብ የሚመጡ እቃዎችን ያለ ምንም ውጣ ውረድ በማስገባት ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ ጋር ቀጠናዊ የንግድ ትስስርን ለማሳደግና ፣ ተባብሮ ለመልማትና ለማደግ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴም ግቡን እንዲመታ ወደቡ ጉልህ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል።

ወደቡ ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ  አማራጭ የገቢና ወጭ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚሆን ጠቁመው፤" በተለይም የክልሉን የግብርና ምርት እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ይረዳል "ብለዋል።

ወደቡ በቀጣይ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥም በአካባቢው የሆቴል፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉለት  የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ  አብራርተዋል።

ትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው "ይህ ወደብ ሀገሪቱ የያዘችውን የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ያግዛል" ብለዋል።

ደረቅ ወደቡም በንግድና ኢንቨስትመንት ለተሰማሩ ድርጅቶች ያለ ምንም ውጣ ውረድ እንዲስተናገዱ በማድረግ የሰሜን ምዕራብ የንግድ ቀጠናውን የሚያነቃቃ እንደሆነ አመልክተዋል።

"በወደቡም ሁሉን አቀፍ የብልፅግና እንቅስቃሴ በማድረግ ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠርም ባለፈ የንግድ እንቅስቃሴው እንዲጠናከር ያግዛል" ብለዋል።

ወደቡ ሀገሪቱ አካታች በሆነ እድገት ወደ ብልፅግና በተገባበት በዚህ ወቅት ተገንብቶ ወደ ተግባር መሸጋገሩ ለግቡ መሳካት እንደሚረዳ ሚኒስትሯ  ተናግረዋል።

ዘመኑ የሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ተሟልቶለት ወደ ተግበራ የገባው የወረታ ወደብ የንግድ ሪፎርሙ እንዲሳካ በማድረግ ብልፅግና እንዲሳካ ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ድህነትን በማስወገድ ወደ ብልፅግና ለመግባት በሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግልም ሁሉም ኃላፊነት ተሰምቶት የድርሻውን እንዲወጣ ወይዘሮ ዳግማዊት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"ወደቡ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ወደ ትግበራ እንዲገባ በተገባው ቃል መሰረት ማከናወን ተችሏል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጰያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሮባ መገርሳ ናቸው ።

ወደቡ 100 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ጠቅሰው " በመጀመሪያው ምዕራፍ በ3 ሄክታር የተገነባው በአንድ ጊዜ 973 ኮንቴነሮችን ያስተናግዳል" ብለዋል።

ሁለተኛው ምዕራፍ  በቀሪ 17 ሄክታር መሬት ላይ በቀጣይ ተገንብቶ ለአግልጋሎት ሲበቃም በዓመት 95 ሺህ 800 ኮንቴነሮችን እንደሚያስተናግድ አስታውቀዋል።

የወረታ ደረቅ ወደብ መገንባትም በሀገሪቱ የሚገኙ ወደቦችን ቁጥር ወደ 8 ከማሳደጉም በላይ የሰሜን ምዕራብ የንግድ ቀጠናውን የገቢና ወጭ ንግድ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓት ወቅት ሚኒስትሮች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የደቡብ ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት የልዑካን ቡድን ተካፍለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም