ግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሃብት ልማትን በማዘመን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

68
አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 7/2012 የእንስሳት ሃብት ልማትን በማዘመን ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመስራት ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ብሄራዊ የእንስሳት ጤና ምርመራና ጥናት ማዕከል ምስረታ 25ኛ የብር ኢዮቤልዩ በዓል ማዕከሉ በሚገኝበት ሰበታ ከተማ እየተከበረ ነው። በዓሉ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን እንደገለጹት፤ የእንስሳት የምርምር ተቋማትን በመደገፍ ዘርፉ ለአገሪቱ ማበርከት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እየተሰራ ይገኛል፡፡ ከውጪ አገር በሚገቡ እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ላይ የሚደረገው የበሽታ ምርመራን በማጠናከር ወደ ሃገር ሊገቡ የሚችሉ በሽታዎችን የመቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ዘርፉ የአገር ኢኮኖሚን እንዲደግፍ የምርት ጥራትን የማስጠበቅና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በቀጣይ ይህን ተግባሩን አጠናክሮ ለመቀጠል የእንስሳት ጤና አገልግሎትን ለማሳደግ በምርምር ማዕከላት የሚገኙ ላብራቶሪዎችን በሙሉ አቅም ለመጠቀም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን እምቅ ሃይል ሚኒስቴሩ የሚጠቀም መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ብሄራዊ የእንስሳት ጤና ምርመራና ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ሩፋኤል እንዳሉት፤ ተቋሙ ባለፉት 25 ዓመታት በእንስሳት ምርምር በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡ በአገሪቷ ለእንስሳት እልቂት ምክንያት የነበረውን የደስታ በሽታ ለመከላከል ሰፊ የጥናት ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል። በቀጣይም ተቋሙ ችግር ፈቺ  የምርምር ስራዎች ላይ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ዶክተር ተስፋዬ ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአካባቢው አርሶ አደሮች በበኩላቸው ማዕከሉ የእንስሶቻቸውን ጤና በመጠበቅ በኩል እያገዛቸው እንደሆነ  አመልክተዋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከልም ወይዘሮ ውድነሽ አባተ ''እንስሳት በበሽታ ሲጠቁ ድጋፍ ይደረግልናል'' ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በ25ኛ ዓመት ክብር በዓል ጎን ለጎን ብሄራዊ የእንስሳት ጤና ምርመራና ጥናት ማዕከል በ74 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው  ከአንድ ሺህ ሰው በላይ የሚይዝ መሰብሰቢያና የስልጠና አዳራሽ ተመርቋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም