መቀሌ 70 እንደርታ ሃዋሳ ከተማን አሸነፈ

54
መቀሌ ኢዜአ የካቲት 07/2012፣- በትግራይ ዓለም አቀፍ ስታድዮም ዛሬ በተካሄደው 14ኛ ሳምንት የፕሪሜር ሊግ ጨዋታ መቀሌ 70 እንደርታ ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ አምስት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸነፈ። የመቀሌ 70 እንደርታ አራት ቁጥር ለብሶ የተጫወተው ኦኪኪ አፎላቢ  በአራተኛው ፣ በ60ኛውና 63ኛው  ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ሶስት ግቦች ሀትሪክ ሰርቷል። 12 ቁጥር ለብሶ የተጫወተው ሙሉጌታ ወልደ ጊዮርጊስ በ12ኛ ደቂቃ እና ቢያድግሊኝ ኤልያስ ደግሞ በ90ኛ ደቂቃ ላይ ጎል በማስቆጠራቸው  ክለቡ በሰፊ ግቦች ልዩነት አሸንፎ ሊወጣ ችሏል። እየተከላከለ በማጥቃት የተጫወተው መቀሌ 70 እንደርታ ክለብ ነጥቡን ከ22 ወደ 25  ከፍ አድርጓል። የሀዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በበኩሉ 17 ቁጥር ለብሶ በተጫወተው ብሩክ በየነ አማካይነት አንድ ግብ አስቆጥሯል። የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ በሰጡት አስተያየት  ጨዋታው ከጠበቁት በላይ በመቀሌ  70 እንደርታ ተበልጠው መሸነፋቸውን ተናግረዋል። የመቀሌ  70 እንደርታ ምክትል አሰልጣኝ ጎይተኦም ኃይሉ በበኩላቸው "በወሳኝ ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይተን አሸንፈን በመውጣታችን ደስተኞች ነን " ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም