መቀሌ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድርን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን አስታወቀ

1392

መቀሌ ሰኔ 20/2010 መቀሌ ዩኒቨርስቲ  ከመጪው እሁድ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚካሄደው የመላው አፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድርን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርስቲው የዘጠነኛው የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር ሰኪሬታሪያትና የዝግጅቱ አስተባባሪ  ዶክተር ከሰተ ለገሰ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ፣ውድድሩን ለማከናወን የሚያስፈልጉ የስፖርት መወዳደሪያ ስፍራዎች፣የእንግዶች ማረፊያ ሆቴሎችና ሌሎችም ማስተናገጃዎች ተመቻችተዋል፡፡

እስካሁን ከ16 በላይ የአፍሪካ ሀገሮች  ዩኒቨርስቲዎች በውድድሩ ለመሳተፍ ፈቃደኝነታቸው ማሳየታቸውን ጠቅሰው ውድድሩ የሚካሄደው በአስር የስፖርት ዓይነቶች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ተወዳዳሪዎችም ከመጪው ዓርብ ጀምሮ መቀሌ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡

ውድድሩን የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ፌዴሬሽን የሚመራው ሲሆን፣ የፌዴሬሽኑ አመራሮች በአሁኑ ወቅት መቀሌ ከተማ መግባታቸው ታውቋል።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ለስፖርት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የመወዳደሪያ ቦታዎችን አስቀድሞ ማዘጋጀቱ  ዶክተር ከሰተ ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ባለው እምቅ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ለውድድሩ አዘጋጅነት እንዲመረጥ ካስቻሉ ምክንያቶች አንዱ ነው።