የማዕከላዊ ጎንደር ደንን ለመንከባከብ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው

207

የካቲት  ኢዜአ 7/2012 ዓ.ም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከ270ሺህ ሄክታር በላይ የሚሸፍን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደንን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እየተካሄደ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡
የመምሪያው ኃላፊ አቶ አንዱአለም ሙሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት ደን የአካባቢውን የስነ ምህዳር ሚዛን በመጠበቅ ፋይዳው የጎላ ነው።

በዞኑ የሚገኘውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደን ለመጠበቅ፣ ለመከባከብና በአጥፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የደን ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል።

ያገገሙ ተፋሰሶች፣ ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖችና አዲስ የሚከለሉ አካባቢዎችን ለማስጠበቅና ለመንከባከብ   ህብረተሰቡ  ተባባሪነቱን እያሳየ ነው።

አቶ አንዱአለም “በዚህም ባለፈው ዓመት 13 ነጥብ አምስት በመቶ የነበረውን የደን ሽፋን ዘንድሮ ወደ 14 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የህብረተሰቡ መነሳሳት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል “ብለዋል።

የተያዘውን የደን ሽፋን ግብ ለማሳካትም በመጪው ክረምት ከ104 ሚሊዮን በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን ለመትከል 15ሺህ የሚጠጉ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ማዘጋጀት ተችሏል።

የሚዘጋጁ  ችግኞችም የተፈጥሮ ሀብት ስራ በተከናወነባቸው 686 ተፋሰሶች፣ የደን ሽፋናቸው እየተመናመነ በመጡ አካባቢዎችና የተራቆቱ ቦታዎችን በመለየት የሚተከል ይሆናል ተብሏል።

“ችግኝ መትከል የህልውና ጉዳይ ነው፤ ደን ከሌለ የሰው ሕይወት አይታሰብም” ያሉት ደግሞ  በኪንፋዝ በገላ ወረዳ የወርቄ ቀበሌ አርሶአደር መላኩ ጀንበሩ ናቸው፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዘመቻ የተከሏቸው  ችግኞች አሁን ላይ ውጤታማ መሆናቸው  ለቀጣይ ልማት እንዳበረታታቸው ተናግረዋል።

ሌላው የዚሁ ወረዳ አርሶአደር አሻግሬ ምትኩ በበኩላቸው ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ የተከለሉ ተፋሰሶች በአጭር ጊዜ አገግመው እየጠቀሟቸው መሆኑን  ገልጸዋል።

“አሁን ላይ ህብረተሰቡ ከጥብቅ ደኖች የእንሳሳት መኖ፣ ለቤት ክዳን የሚሆን ሳርና ሌሎች ጥቅሞችን በቀጥታ እያገኘ በመሆኑ ደኑን ገንዘብ በማዋጣትና ጥበቃ በመቅጠር ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አይልም “ብለዋል።፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባለፈው የክረምት ወቅት በአንጓዴ አሻራና መደበኛ ፕሮግራም  ተተክለው ከነበሩት 77 ሚሊዮን 500ሺህ   ሀገር በቀል ችግኞች ውስጥ በተካሄደ ቆጠራ 85 በመቶ መጽደቁ የግብርና መምሪያው አመልክቷ።