ኢትዮጵያዊያን በ”ዱባይ ኤክስፖ 2020″ ግንባታ ላይ የስራ ዕድል አገኙ

180

አዲስ አበባ የካቲት  7/2012 ዓ.ም (ኢዜአ)ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በ”ዱባይ የዓለም ኤክስፖ 2020″ ግንባታ ላይ 10 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ የስራ ዕድል አመቻቹ።
ከዚህ በተጨማሪ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ትምህርት ቤት እንዲከፈትም ፈቃድ አግኝተዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያዩት ችግረኛ ኢትዮጵያዊያን መፍትሄ እንደሚያገኙም ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግስት ቃል እንደተገባላቸው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በአምስት ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ እየተገነባ ያለውን “ዱባይ ኤክስፖ 2020″ን ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅትም 10 ሺህ ኢትዮጵያዊያን በግዙፉ የዱባይ የዓለም ኤክስፖ 2020 ግንባታ ላይ እንደሚሳተፉ ይፋ ሆኗል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በኤክስፖው ላይ ራሷን እንድታስተዋውቅ በግዙፍ አዳራሽ ውስጥ ቦታ እንደተመቻቸላትም ተገልጿል።

የዱባይ የዓለም ኤክስፖ 2020 ዋና ዳይሬክተር ሪም አል-ሐሺሚ ኢትዮጵያ የተባበሩት የዓረብ ኤሚሬቶች ግንባር ቀደም አጋር መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው ኤክስፖ ላይ ለመሳተፍና ‘ምድረ-ቀደምት’ በሚል ርዕስ አውደ-ርዕይ ለማሳየት ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች።