የከተማ አስተዳደሩ ያስገነባው የአስፓልት መንገድ ተመርቆ ለተሽከርካሪ ክፍት ሆነ

322

መቀሌ ኢዜአ የካቲት 7/2012፡- የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ያስገነባው የአምስት ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ ዛሬ ተመርቆ ለተሽከርካሪ ክፍት ሆነ።

መንገዱን መረቀው  ለተሽከርካሪ ክፍት ያደረጉት የትግራይ ክልል  ምክትል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልና የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር አርአያ ግርማይ ናቸው።

ምክትል ከንቲባው በምረቃው ስነስርዓት ንደገለጹት ዛሬ የተመረቀው የአምስት የአስፓልት መንገድ በግንባታ ሂደት ላይ ካለው  71 ኪሎ ሜትር ውስጥ የተጠናቀቀው ነው።

የተጠናቀቀው ጨምሮ ለ71 ኪሎ ሜትሩ መንገድ የተያዘለት በጀት  አራት ቢሊዮን 500 ሚሊዮን እንደሆነም አመልክተው  ለዚህም  ወጪ የሚሸፈነው በረጅም ጊዜ በሚከፈል የብድር ገንዘብ መሆኑን አስረድተዋል።

የተጠናቀቀው መንገዱ በከተማው የተለያዩ አከባቢዎች ባለፈው ዓመት ግንባታው ተጀምሮ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የመንገዱ  መገንባት በከተማው የሚታየውን የተሽከርካሪ  መጨናነቅ የሚቀንሰው ከመሆኑም በላይ ለከተማው እድገት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ኢንጂነሩ ተናግረዋል።

ዶክተር ደብረፅዮን በበኩላቸው” የአስፓልት መንገዱ ግንባታ ክልሉ ከድህነት በፍጥነት ለመውጣት በመሰራት ላይ ከሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው “ብለዋል።

ህዝቡ የፀረ ድህነት ተጋድሎው አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከአስፓልት መንገድ በተጨማሪ በከተማ አስተዳደሩ ፊት ለፊት የተገነባ አደባባይም ተመርቀዋል።

የአስፓልት መንገዱ ለአገልግሎት መብቃቱ በከተማው ይታይ የነበረው የተሽከርካሪ መጨናነቅ ችግር በማቃለል  የትራፊክ ፍሰቱ እንዲቀላጠፍ የሚረዳ መሆኑን  የከተማው ነዋሪ ሐጂ መሀመድኑር በሽር ተናግረዋል።

በአደባባዩ አቅራቢያ የወጣቶች መዝናኛ ስፍራ የተሰራ ሲሆን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩና ሌሎች እንግዶች በቦታው ችግኝ ተክለዋል።