በሱዳን የገዳሪፍ ግዛት ልዑካን ቡድን በባህርዳር ከተማ አቀባበል ተደረገለት

199

ባህርዳር ኢዜአ የካቲት 7/2012፡  በሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ገዥ በሜጀር ጀኔራል ነርሰዲን አብዱል የተመራ የልዑካን ቡድን ባህርዳር ከተማ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት።
በአቀባበል ስነ ስርዓት  ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የክልልና የፌደራል አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  ዶክተር መሃሪ ታደሰ በአቀባበል ስነስርዓት ወቅት  እንዳሉት ኢትዮጵያና ሱዳን ለዘመናት የቆየ መልካም ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።

ሁለቱ ሃገራት በሰላምና ጸጥታ፣ በመሰረተ ልማት፣ በወደብና ሌሎች ጉዳዮች በጋራ በመስራት የህዝባቸውን ጥቅም እያረጋገጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በተለይም የገዳሪፍ ግዛት ከአማራ ክልል ጋር በድንበር የሚዋሰኑ በመሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱ የጠነከረ መሆኑንም አስረድተዋል።

ይህን ግንኙነት ወደ ህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማሳደግ የተከናወነው ስራ ውጤታማ ለመሆኑ የልዑካን ቡድኑ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል።

ቡድኑ በሁለት ቀናት ቆይታውም በባህርዳር ከተማና አካባቢው የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችን፣ የልማት ስራዎችንና ሌሎች ቦታዎችን እንደሚገበኙ ይጠበቃል።

“ይህም የእርስ በእርስ ተሞክሮና ልምድን በመለዋወጥ ለጋራ ግንኙነትና ልማት ዘላቂነት ያለው አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ” ሲሉ ዶክተር መሃሪ ገልጸዋል።

ከሱዳን ገዳሪፍ ግዛት የመጣው የልዑካን ቡድን 20 አባላትን ያካተተ ነው።