መጪው ምርጫ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ የደረሰችበትን ደረጃ ለዓለም የምታሳይበት ይሆናል---በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር

89
አዲስ አበባ  (ኢዜአ ) የካቲት 7/2012 መጪው ምርጫ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲን እውን ማድረጓን ለተቀረው ዓለም የምታሳይበት እንደሚሆን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኪ ማቱሳንጋ ገለጹ ። አገራቸው ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ እንዲሆን የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክርም አረጋግጠዋል። አምባሳደር ዳሱኪ ማቱሳንጋ ለኢዜአ እንዳስረዱት፤ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የምታደርገው ምርጫ እየተገበረች ያለችው ዴሞክራሲ የደረሰበትን ደረጃ ለሌላው ዓለም ታሳይበታለች ተብሎ ይታመናል። ጃፓን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫው የህዝብ አመኔታን ያተረፈ ለማድረግ፣ ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አለመግባባቶች ለመፍታትና የመራጮች ትምህርት በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል። ''ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የምናደርገው ድጋፍ ይቀጥላል። የምርጫው ውጤትም በፖለቲካ ፓርቲዎችና በባለድርሻ አካላት ተቀባይነት ይኖረዋል'' በማለትም አምባሳደር ማቱሳንጋ የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል። ጃፓን የምርጫውን ሂደት ለማገዝና ለምርጫ ቁሳቁስ መግዣ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ  በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲ ፒ) በኩል መለገሷን ተናግረዋል። አገራቸው ለምርጫው ከምታደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ለጅማ-ጭዳ መንገድ ግንባታ የ100 ሚሊዮን ዶላርና ለሴት ስራ ፈጣሪዎች መንቀሳቀሻ የሚውል የ500 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጓን አስታውሰዋል። ኢትዮጵያና ጃፓን ለ90 ዓመታት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም