በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታ መስፋፋት ኢኮኖሚያዊ አቅምን ያጠናክራል --- የውጭ ጋዜጠኞች

61

አዲስ አበባ  (ኢዜአ ) የካቲት 7/2012 በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታ መስፋፋቱ ኢኮኖሚያዊ አቅምን እንደሚያጠናክር የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ገለጹ።

ኢዜአ የአፍሪካ ኅብረት 33ኛ የመሪዎች ጉባዔን ለመዘገብ የመጡ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ስለ ኢትዮጵያ ያላቸውን ምልከታ አስመልክቶ አነጋግሯቸዋል።

በቻይና ሬዲዮ ኢንተርናሽናል የሚሰራው ሮናልድ ሙትዬ ኢትዮጵያን ለ10 ተከታታይ ዓመታት ሲጎበኝ ለውጥ እንደሚመለከት ገልጿል።

የመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ ዕድገቷ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ እንደሆነና የኢኮኖሚ ዕድገቷንም እንደሚያመለክት ነው የተናገረው።

በአዲስ አበባ የዘመናዊ የመኖሪያና የቢዝነስ ተቋማት ግንባታ መመልከቱን ያወሳው ጋዜጠኛው፣ የአገሪቷ ከተሞችም እያደጉ መምጣታቸውን አንስቷል።

ከሶስት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የኦንላይን የታክሲ አገልግሎት እንዳልነበረ ያስታወሰው ሙትዬ፣ አሁን አገልግሎቱ መጀመሩ አገሪቷ ዓለም የደረሰበት ደረጃ መድረሷን ያሳያል ብሏል።

የአሊ ባባ ኩባንያ መስራችና ባለቤት ጃክ ማ ኢትዮጵያን መጎብኘቱ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ በሯን መክፈቷን ያመላክታል ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት አንዷ እንደሆነች የገለጸው ጋዜጠኛ፣ የትምህርት ጥራትን ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነም ተናግሯል።

የደቡብ አፍሪካው ኦንላይን ዕለታዊ ጋዜጣ ዴይሊ ማቭሪክ የውጭ ጉዳዮች ተንታኝ ፒተር ፋብሪሺየስ፤ "ዘንድሮ ኢትዮጵያን ለስድስተኛ ጊዜ እየጎበኘኋት ነው" ብሏል።

በኢትዮጵያ እየተካሔደ ያለው የመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ በቀጣዩ ትውልድ ላይ መዋዕለ ንዋይዋን እያፈሰሰች መሆኑን እንደሚያመላከትም ይገልጻል።

ኢትዮጵያ የውጭ ጉብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ የቱሪዝም አገልግሎት አሰጣጧን ማሻሻል እንደሚገባትም ጠቁሟል።

የሞዛምቢክ ጠቅላይ ሚኒስትር የፎቶ ግራፍ ባለሙያና ጋዜጠኛ ካርሎስ ኬዩ ደግሞ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኛት ከሦስት ዓመታት በፊት እንደነበር ያስታውሳል።

የመሠረተ ልማት ግንባታ መስፋፋት የአንድን አገር ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ እምነቱን ገልጿል።

ወደ ኢትዮጵያ ዳግም ስመጣ የአዲስ አበባን ዕድገት አመላካች የሆኑ ሕንጻዎችን ተመልክቻለሁ ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም