የአፍሪካ መሪዎች ግጭቶችን ለመፍታት ለዜጎች ፍላጎት ምላሽ መስጠት አለባቸው – የውጭ አገራት መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች

832

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 7/2012 የአፍሪካ መሪዎች ግጭቶችን ለመፍታት መልካም አስተዳደር ማስፈንና ለዜጎች ፍላጎት ተገቢው ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው የውጭ አገራት መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ገለጹ።

“የጦር መሳሪያ ድምጽን በማጥፋት ለአፍሪካ ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠር” የሚል መሪ ሃሳብ ያለው 33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በቅርቡ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።

ኢዜአ ይህን የኅብረቱን ጉባዔ መሪ ሃሳብ አስመልክቶ የውጭ አገራት መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞችን አነጋግሯል።

የደቡብ አፍሪካ ኦንላይን ዕለታዊ ጋዜጣ የውጭ ጉዳዮች ተንታኝ ፒተር ፋብሪሺየስ የአፍሪካን ሠላምና ደህንነት በዘላቂነት ማረጋገጥ ከተፈለገ አገራት መልካም አስተዳደር ማስፈንና የዴሞክራሲ ስርዓትን ማጎልበት ይገባቸዋል ሲል ገልጿል።

በአፍሪካ የጦር መሣሪያ ድምጽ እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም ብዙ ግጭቶች መኖራቸውን ጠቅሶ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቀጣናው ሠላም ለማስፈን የጀመሩት ስራ መልካም የሚባል ነው ብሏል።

የአፍሪካ መንግሥታት የዜጎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ማክበርና እልቂት የሚያስከትሉ ግጭቶች እንዲፈጠሩ ከማድረግ መቆጠብ እንዳለባቸውም አመልክቷል።

የፓርቹጋል የዜና ወኪል ሉሳ ጋዜጠኛ ክርስቲና ፈርናንዴዝ ደግሞ በአፍሪካ ግጭቶችን ለመፍታት የአገራቱ መሪዎች ለዜጎች ፍላጎት ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይገባቸዋል ትላለች።

የአፍሪካ አገራት መሪዎች ግጭቶችን ማስቆምና ሠላምን ማስፈን ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ሊሆን እንደሚገባም ገልጻለች።

በአፍሪካ ላሉ ግጭቶች በአጭር ጊዜ መፍትሔ ማምጣት እንደማይቻል ጠቅሳ በአህጉሪቷ በዘላቂነት ሠላምና ደህንነት ለማምጣት አፍሪካዊያውን በጋራ መስራት እንዳለባቸው አክላለች።

አፍሪካዊያን ችግራቸው በሌላ አካል እንዲፈታላቸው መጠበቅ የለባቸውም፤ የአፍሪካ ችግሮች የሚፈቱት በአፍሪካዊያን ብቻ ነው ያለው ደግሞ የሞዛምፒክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፎቶ ግራፍ አንሺና የፎቶ ጋዜጠኛ ካርሎስ ኬዩ ነው።

በአፍሪካ የጦር መሳሪያን ድምጽ ለማጥፋት መሪዎች በቃል የሚናገሩትን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባቸውም ተናግሯል።

በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ውይይት የተደረገባቸው ብዙ አጀንዳዎች በአግባቡ ተተግብረውና መሬት ላይ ወርደው ለውጥ ሊያመጡ ይገባል ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።