ኅብረቱ የአስቸኳይ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ለማቋቋም የሚያስችል ንድፈ ሃሳብ ለአባል አገራቱ አቀረበ

77
አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 7/2012 የአፍሪካ ኅብረት የአስቸኳይ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ለማቋቋም የሚያስችል ንድፈ ሀሳብ ለአባል አገራቱ ማቅረቡን ገለጸ። ፈንዱ ተግባራዊ የሚሆነው አባል አገራቱ ሲስማሙ እንደሆነም ተመልክቷል። አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላት ተጋላጭነትና በለውጡ በሚከሰቱ አደጋዎች ከፍተኛ ተጎጂ እንደሆነች ይገለጻል። የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖው የአፍሪካን ዜጎች ኑሮ የማሻሻልና የኢኮኖሚ ልማት ስራዎች በሚፈለገው መልኩ እንዳይሄዱ እክል እየፈጠረ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዎች በለውጡ የሚደርሱ አደጋዎችን የመቋቋምና የመከላከል አቅማቸው አነስተኛ እንደሆነና ለአቅም ማነሱ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው የፋይናንስ እጥረት እንደሆነ ያነሳሉ። የአፍሪካ ኅብረት የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽነር ሚስ ጆሴፋ ሳኮ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚያስችላት ፈንድ ለማቋቋም የኅብረቱ ንድፈ ሀሳብ ለአገራቱ መቅረቡን ለኢዜአ ገልጸዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.አ.አ በ2015 'ኮፕ 21' በሚል ስያሜ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ባካሄደው ስብስባ አገራት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ይታወቃል። ከስምምነቱ አንዱ ያደጉ አገራት እ.አ.አ እስከ 2025 በየዓመቱ አፍሪካን ጨምሮ በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርስባቸውን አደጋዎች ለመቋቋምና ለመላመድ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ መስጠት ነው። እንደ ጆሴፋ ሳኮ ገለጻ፤ ተግባራዊ በሆነው የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ቃል ከተገባው ገንዘብ የተገኘው ሃብት ውስንና ለሚደርሱት ችግሮችም ምላሽ የሚሰጥ አይደለም። በአየር ንብረት ለውጡ እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎች በአፍሪካ ያለውን የምግብ ደህንነት ለማረጋገጥ እየተከናወነ ባለው ስራ ላይም እክል መፍጠሩን አንስተዋል። በአፍሪካ ሰብዓዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ ልዩ ፈንዶች መኖራቸውንና አህጉሪቷ አሁን እየገጠማት ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም የአስቸኳይ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ማቋቋም በጣም አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነም አመልክተዋል። የአፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ለሚያስችሉ ስራዎች ከዓመታዊ በጀታቸው ሁለት በመቶ የሚሆነውን እያዋሉ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ይህም በዘላቂነት መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም