በወላይታ ዞን የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

496

ሶዶ ኢዜአ የካቲት 7/2012 ፡- በወላይታ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ዳግም የተከሰተው የአንበጣ መንጋ የበልግ እርሻ ላይ የከፋ አደጋ ሳያስከትል ለመከላከል ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
በዞኑ የበረሃ አንበጣ ዳግም ከተከሰተባቸው ወረዳዎች ከጋሞ ዞን የሚያዋስነው የአባላ አባያ ወረዳ አንዱ ሲሆን በዚሁ አካባቢ ባለ ሰፋፊ የእርሻ የኢንቨስትመንት ልማት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የወረዳው እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይስሃቅ መና እንዳሉት የአንበጣ መንጋው በወረዳው አባላ ሾያ፣ ማራቃ፣ ቆልሾቦና ዘግሬ ቀበሌዎች ተከስቷል።

“የተለያዩ የዘፍ ዝርያዎችን፣  አኩሪ አተር፣ ሃላኮና ሌሎች ተክሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው “ብለዋል፡፡

ህዝቡ በባህላዊ መንገድ እየተከላከለ ቢሆንም ከአንድ ቦታ ሲያባርሩት ተመልሶ እየመጣ ከአቅም በላይ በመሆኑ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ከተከሰተ ጀምሮ ህዝቡ  የአንበጠ መንጋውን ባህላዊ መከላከል ዘዴ  ለመከላከል ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከአቅም በላይ በመሆኑ  በዚሁ ከቀጠለ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምህረቱ ሣሙኤል ናቸው፡፡

“በአውሮፕላን በመታገዝ የኬሚካል  ርጭት ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት እየተነጋገርን ነው” ብለዋል፡፡

ቅድመ ትንበያ መረጃ በመስጠትና በማስተማር እንዲሁም ባለሙያዎችና የመገናኛ ብዙሀን አካላት ግንዛቤ በመፍጠር የድርሻቸውን  መወጣት እንዳለባቸው አመልከተዋል።

የአንበጣ መንጋ ከትላንት በስቲያ ጀምሮ በዱጉና ፋንጎ፣ ሁምቦ፣ አባላ አባያ፣ ዳሞት ጋሌና ሌሎች  ወረዳዎች ዳግም መከሰቱን  የወላይታ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አሞና ቶልካ አስረድተዋል።

ከ15 ቀናት በፊት ተከስቶ   ህዝቡ ባደረገው የባህላዊ መከላከያ ዜዴ ሸሽቶ እንደነበረ አስታውሰው  በአውሮፕላን በመታገዝ የኬሚካል ርጭት ለማድረግ አካባቢን  የመለየት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ አሞና እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው የነፋስን አቅጣጫ ተከትሎ እስከ ሰኔ ወር ድረስ ሊዘለቅ  እንደሚችል ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች እያመለከቱ ነው።።

አሁን ላይ የበልግና ሁለተኛ ዙር የመስኖ እርሻ በከፍተኛ ሁኔታ እየለማ ያለበት ወቅት በመሆኑ አርሶ አደሩና የሚመለከታቸው አካላት ባላቸው አቅም ሁሉ በትኩረት እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በወረዳው የማራቃ ቀበሌ አርሶ አደር ሶርሣ ሌራ በሰጡት አስተያየት መንጋው ከትላንት በስቲያ  ጀምሮ መከሰቱን ገልጸው የተለያዩ ድምጾችን በማሰማትና ጭስ በማጨስ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት   አካባቢው ካለው አረንጓዴነት የተነሳ አንበጣው ብዙም እየሸሸ ባለመሆኑ ተስፋ ሳይቆርጡ እየተከላከሉ ይገኛሉ፡፡

ለፍተው ያለሙትን እርሻ ከጥቅም ውጪ አድርጎ ለጉዳት እንዳይዳርግ ስጋት እንዳላቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ መንግስት  በኬሚካል ርጭት ድጋፍ እንዲያድርጋለቸው መፈለጋቸውን ገልጸዋል።

ክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋው  ህብረተሰቡ በባህላዊ ዘዴ እየተከላከለ እንደሚገኝ የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አመልክቷል።

እስካሁን በአይሮፕላን በመታገዝ ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን አካባቢዎች ላይ ኬሚካል መረጨቱን ጠቁሟል።