ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሼህ መሃመድ ቢን ረሺድ አመልከቱም ጋር ተወያዩ

117

አዲስ አበባ  (ኢዜአ ) የካቲት 7/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የዱባይ ገዢ ሼኸ መሃመድ ቢን ረሺድ አመልከቱም ጋር ተወያዩ።

የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንዳሉት፤ ውይይቱ በዋናነት ያተኮረው በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ 300 ከሚደርሱ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ተወካዮች ጋር ባካሄዱት ውይይት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተውላቸዋል።

ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከዱባይ ገዥ ጋር በነበራቸው ውይይትም በአገሪቷ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተለይም ደግሞ ሴቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርገው መክረዋል።

ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የአምልኮ ስፍራ የሚገነቡበት ሁኔታና የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤቶች ማቋቋምም የውይይታቸው አጀንዳዎች እንደነበሩም አቶ ንጉሱ ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው ለውጥ ከአገር ባለፈ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ብሩህ ተስፋ እንዳለው መግለጻቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀመሩትን ለውጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉም መክረዋል።

በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውንም ነው አቶ ንጉሱ ያወሱት።

በዱባይ የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች የአምልኮ ስፍራ እንዲገነቡ ፈቃድ መስጠቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውንም ነው የገለጹት።

በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ አገራት ከሚኖሩ ሴት ኢትዮጵያዊን ጋር እንደሚመክሩ አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።

የውይይቱ ዓላማም ሴቶቹ በሚገጥሟቸው ማኅበራዊ ችግሮች ላይ መፍትሄ ማበጀት መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በውይይቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ሴት ሚኒስትሮች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም