በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተለያዩ ክለቦች ተጫዋች የነበረዉ ሞገስ ታደሰ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈፀመ

64
አዲስ አበባ ጥር 6/2012  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተለያዩ ክለቦች ተጫዋች የነበረዉ የቀኝ መስመር ተጨዋች ሞገስ ታደሰ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈፀመ። የተጫዋቹ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በቀጨኔ ደብረ ሰላም መድሃኒዓለም ወዳጅ ዘመዶቹ እና የስፖርቱ ቤተሰብ በተገኙበት ተፈጽሟል። ተጫዋቹ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የ17 ዓመት በታች ቡድን ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የተጫወተ ሲሆን ከ20 ዓመት በታች ለወጣት ቡድኑ እንዲሁም ለዋናው ቡድን በመሰለፍ ብዙ ድሎች ተቀዳጅቷል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከተለያየ በኋላም በሲዳማቡና፣ አዳማ ከተማ፣ ወልድያ ከተማና በኢትዮ ኤሌትሪክ ተጫዉቷል። ህዳር 5 ቀን 1983 ዓ.ም የተወለደዉ ሞገስ ታደሰ እግር ኳስ መጫወት የጀመረዉ ተወልዶ ባደገበት ጃንሜዳ አካባቢ ሲሆን በአሰልጣኝ አለባቸዉ ኪዳኔ 'ኬር ስኩዌር' በሚባል የታዳጊ ቡድን በመጫወት ነበር የጀመረዉ። በዚህም ቡድን ሲጫወት ቆይቶ በ1999 ዓ.ም በየአካባቢዉ ታዳጊዎች በተስፋ ቡድኑ ለማካተት በሚያደርገዉ ምልመላ ቅዱስ ጊዮርጊስን መቀላቀል ችሏል። ሞገስ በቅዱስ ጊዮርጊስ በፍጥነት ባሳየዉ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በ2001 ዓ.ም ላይ በዋናዉ ቡድንና ተስፋ ቡድኑ እየተመላለሰ ሲጫወት ቆይቶ በ2002 ከዋናዉ ቡድን ጋር ተቀላቅሏል። ሞገስ ታደሰ ባለትዳርና  የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም