ስምንት የልህቀት ማእከላት ያካተተው የጥናትና ምርምር ፓርክ በቅርቡ ስራ ይጀምሯል

1984

አዳማ  የካቲት 06/2012 (ኢዜአ) የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በ445 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚያስገነባው ስምንት የልህቀት ማእከላትን ያካተተው የጥናትና ምርምር ፓርክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባራዊ ስራ ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ ።

የዩኒቨርሲቲው የግንባታ ፕሮጄክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ   አቶ ሸዋንግዛው ዳቢ ለኢዜአ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው የተደራጁ  የምርምር ስራዎችን የሚያካሔዱ ስምንት  የልህቀት ማእከላትን ያካተተው የጥናትና ምርምር ፓርክ በመጪው አዲስ የበጀት ዓመት ስራ ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ ነው ።

ግንባታው 97 በመቶ የደረሰው የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ፓርክ በተለይ በህዋ ሳይንስ፣በኢንጅነሪንግ ፣በፋርማቲካል ፣በማኑፋክቸሪንግ ፣በተሽከርካሪ ሞተር ማምረት፣በሲሚንቶና በውሃ ሀብት ዘርፍ የሚካሔዱ ጥናቶችና ምርምሮች በተሳካ መልኩ ለማከናወን ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል ።

የጥናትና ምርምር ፓርኩ የዲዛይንና የግንባታ ጥናት የተከናወነው በኮሪያ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ኢንጅነሮች መሆኑንም ስራ አስኪያጁ  ገልፀዋል።

የምርምር ፓርኩ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ከመሆኑን ባለፈ የሀገሪቷን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍን  ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግር  መሆኑን አቶ ሸዋንግዛው ተናግረዋል።

ፓርኩ በ445 ሚሊዮን ብር በ2006 ዓ.ም መጨረሻ የተጀመረ ቢሆንም በተደጋጋሚ በተደረገበት የዲዛይንና የግንባታ ለውጥ በወቅቱ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት አልቻለም ነበር ብለዋል።

በዋናነት የዲዛይን ማሻሻያ ያስፈለገው ከስምንቱ የልህቀት ማእከላት ጋር የጥናትና ምርምር ፓርኩን ለማገናኘትና ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን እንደሆነ ተናግረዋል።

በፓረኩ  ምርምር የሚያካሂዱ 60 ተማራማሪዎችና ሳይንትስቶች ይኖራሉ ብለዋል።

ተመራማሪዎቹ ሙሉ ጊዜያቸውን በጥናትና ምርምር ብቻ ላይ እንዲያደርጉና ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውኑ የተሟላ መኖሪያ ቤት ፣ ጂምናዚየምና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የተሰራላቸው መሆኑንም አቶ ሸዋንግዛው ተናግረዋል ።

የግንባታው ሥራ ተቋራጭ ዋና መሃንዲስ ኢንጅነር ዳንኤል አለማየው በበኩላቸው የፓርኩን የግንባታ ጥራት ለማስጠበቅና ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላ እንዲሆን በተደረገው የዲዛይን ለውጥ መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ መዘግየቱን ገልጠዋል።

በሀገሪቷ የነበረው የውጪ ምንዛሪ እጥረት የኤሌክትሮ መከናኒካል ሥራችን በአግባቡ እንዳናከናውን ተጨማሪ እንቅፋት ሆኖብን ነበር ብለዋል።

ይህን ችግር በዩኒቨርሲቲው የቦርድ አመራሮች ጥረትና በመንግስት ቁርጠኝነት  በመፈታቱ በአሁኑ ወቅት ጥቃቅን የማጠናቀቂያ ስራዎች ብቻ እንደቀሩት አስረድተዋል ።

የግንባታ ሥራው በኮሪያና በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች እየተገመገመ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ መካሔዱንም ከመሃንዲሱ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።