ምርጫ ቦርድ የሚዲያ ሞኒተሪንግ ቡድን ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ነው

67
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 6/2012 ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመገናኛ ብዙሃን በሚደረግ የምርጫ ዘመቻ የሚፈጠር የስነ-ምግባር ጥሰትን መከላከልና ለመራጮች መረጃ መስጠት የሚያስችል የሚዲያ ሞኒተሪንግ ቡድን ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገለጸ። ቦርዱ ከምርጫ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ማድረስ የሚያስችል የሚዲያ ማዕከል ሊያቋቁም መሆኑንም አስታውቋል። ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሁለተኛውን የምርጫ ባለድርሻ አካላት ኮንፍረንስ እያካሄደ ነው። በኮንፍረንሱ እንደተባለው የሚዲያ ሞኒተሪንግ ቡድኑ በምርጫ ወቅት መረጃዎችን ለመሰብሰብና የቦርዱን ውሳኔዎች ተፈፃሚ ለማድረግ እንዲረዳ ሆኖ ይቋቋማል። የሚቋቋመው የሚዲያ ማዕከልም ከመገናኛ ብዙሃን፣ ከሲቪል ማህበራትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን መረጃ የሚሰጥበት እንደሆነ ተገልጿል። የቦርዱ ድህረ ገጽ ተሰርቶ እንደተጠናቀቀም መረጃዎች ተደራሽ ይሆናሉ ነው የተባለው። በቦርዱ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ እየተሰጠ ያለው ወቅታዊ መረጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ መዋቅሩን በአዲስ መልክ በማደራጀት ገለልተኛ፣ ግልፅና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ስትራቴጂክ ግቦችን በመቅረጽ የዝግጅት ስራ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። ከሚያስፈልገው የሰው ሃይል ያለው 60 በመቶው ብቻ እንደሆነ የገለጸው ቦርዱ ከዚህም ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ በክልል ቅርንጫፎች እንደሚገኝ ገልጿል። በክልል ቅርንጫፎች የሰው ሀይል ለሟሟላት ቅጥር እየተፈፀመ እንደሆነና በሰባት ቅርንጫፎች ቅጥር ተፈጽሞ ሠራተኞች ስራ መጀመራቸው፤ በአራት ቅርንጫፎች የተቀጠሩም በቅርቡ ስራ እንደሚጀምሩ ተመልክቷል። የቦርዱን ሠራተኞች በክህሎትና በዕውቀት ለማጎልበት የሚሰጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም እየተካሄደ በሚገኘው ኮንፍረንስ ተጠቁሟል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም