በጋሞ ዞን ባለሃብቶች ከ5 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ ዕድል ፈጠሩ

67
አርባምንጭ፣ የካቲት 6/2012 (ኢዜአ) በጋሞ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ዘርፎች ወደ ስራ የገቡ ባለሃብቶች ከ5 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አዲሱ ሰጠኝ ለኢዜአ እንደገለጹት የስራ እድሉን ያስገኙት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የገቡ 192 ባለሃብቶች ናቸው። የመስሪያ ቦታ ተመቻችላቸው ወደ ስራ የገቡት  እነዚህ ባለሀብቶች በግብርና ፣ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው። ባለሀብቶቹ  በተጨማሪም  የአካባቢው አርሶ አደር የሚያመርተውን የግብርና ውጤት በመረከብ እሴት እየጨመሩ ለገበያ በማቅረብ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአካባቢው በማስተዋወቅ እንዲሁም  የመብራትና የመንገድ መሰረተ ልማት በማመቻቸት  ህብረተሰቡ እንዲጠቅምባቸው እያገዙ ናቸው። እስካሁንም 23 ኪሎ ሜትር ጥርጊያ መንገድ ፣ ለ35 አርሶ አደሮች በጸሐይ ኃይል የሚሰራ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከማመቻቸታቸውም ሌላ  በዳራማሎ ወረዳ ለአንድ ትምህርት ቤት ግንባታ 600ሺህ ብር መድበው እየሰሩ ያሉት ይገኙበታል። ባለሃብቶቹ የሚንቀሳቀሱት በአርባምን፣ ጨንቻ፣ ሰላም በርና ከምባ ከተሞች እንዲሁም አርባምንጭ ዙሪያ፣ ምዕራብ አባያ፣ ዳራማሎ እና ቁጫ ወረዳዎች ውስጥ መሆኑ ተመልክቷል። በአርባ ምንጭ ከተማ የተሰማሩት የዓባያ ዱቄት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ መቆያ ገብረጊዮርጊስ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው ያለውን ሰላማዊ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል። ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ከዳቦ ዱቄት ጋር ተያይዞ ያለውን እጥረት ለማቃለል እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። የዴሪክ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት አቶ ሚልኪያስ አዴቦ በበኩላቸው በ24 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ በቅርቡ ወደ ስራ በገባው ሆቴል ለ42 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል። የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ባደረገላቸው ድጋፍ   በቀጣይ የማስፋፊያ ግንባታ በማድረግ ተጨማሪ የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰሩም ጠቁመዋል። ወጣት ዓለሙ ሀታ በሰጠው አስተያየት በዓባያ ዱቄት ፋብሪካ  በወር 3 ሺህ ብር ደመወዝ እየተከፈለው በተፈጠረለት የስራ እድል  አቋርጦት የነበረውን ትምህርቱን በማታ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል። በዴሪክ ኢንተርናሽናል ሆቴል  በተመቻቸው የስራ  እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ  ሌላው የአካባቢው ነዋሪ  አቶ ፍቃዱ ሳልልኝ ናቸው። "በአካባቢው ያለው የተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ ባለሀብቶች እንዲመጡ ያደረገ በመሆኑ  ሰላማዊ ሁኔታው እንዲቀጥል የበኩላችንን እንወጣለን" ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም