ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከየትኛውም አካል ተጽዕኖ ቢኖርም ብሄራዊ ጥቅሟን ያላሰጠበቀ ስምምነት እንደማትፈርም ተገለፀ

102
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 6/2012 ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከየትኛውም አካል ተጽዕኖ ቢኖርም ብሄራዊ ጥቅሟን ያላሰጠበቀ ስምምነት እንደማትፈርም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰተዋል። በመግለጫቸው በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ፣ የሁለትዮሽ ውይይቶች እና በዋሽንግተን ዲ.ሲ. በህዳሴ ግድብ ላይ እየተደረጉ ያለው ውይይትን ጨምሮ በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ እየተሰራ ስላለው ስራ አብራርተዋል። ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ሲያደርጉት የነበረውን ድርድርና የረቂቅ የስምምነት ሰነድ ዝግጅት ሳይቋጭ መጠናቀቁ ይታወቃል። በድርድሩ ሱዳን የአቋም ለውጥ አድርጋ ከግብጽ ጋር መወገኗን እንዲሁም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለግብጽ መወገናቸውን አሁን ላይ ጉዳዩ "4 ለ 1" ሆኗል የሚሉና በዚህም ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ እንደሆነ በመግለጽ የኢትዮጵያ አቋም ምን እንደሆነ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ተነስቷል። በዚህም ቃል አቀባዩ አቶ ነቢያት በሰጡት ምላሽ፤ በግድቡ ዙሪያ ከየትኛውም አካል ተጽዕኖ ቢኖር ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥና መርህ ላይ የተመሰረተ ጥቅሟን ያስጠበቀ ድርድር እንደምታራምድ አረጋግጠዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥ ነው አጽኖኦት የሰጡት። በዋሽንግተን ዲ.ሲ. በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማዘጋጀት ሲካሄድ የነበረው ውይይት በዚህኛውም ዙር ሳይቋጭ ትናንት ማማምሻውን መጠናቀቁ ይታወሳል። የኢትዮጵያ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በዚህ ሳምንት የሶስቱ አገሮች የህግ ባለሙያዎች የደረሱበትን ረቂቅ ስምምነት ዝግጅት በኢትዮጵያ በኩል ለመገምገም ወደ ስፍራው ማቅናታቸውም እንዲሁ፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም