በትግራይ ክልል የ600 ኪሎ ሜትር ጠጠር መንገድ ግንባታ እየተካሔደ ነው

53
ሽሬ ኢዜአ የካቲት 06/12 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ዘንድሮ 600 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ኮንስትራክሽን፣መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። የመንገዶቹ ግንባታ እየተከናወኑ ያሉት የክልሉ መንግስትና ህዝብ በመደቡት 152 ሚሊዮን ብር ወጪ ነው ተብሏል ። የመንገዶቹ ግንባታ አንድ አካል የነበረው በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በላዕላይ ዓድያቦ ወረዳ የተሰራው 15 ኪሎ ሜትር የመኪና መንገድ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። የክልሉ የኮንስትራክሽን፣መንገድና ትራስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ገብረጻድቅ  በምረቃው ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንዳሉት መንገደቹ ሲጠናቀቁ በክልሉ ውስጥ ያሉትን 45 የገጠር ቀበሌዎችን እርስ በራሳቸው እንዲገናኙ የሚያደርጉ ናቸው። በተጨማሪም ከዋና ዋና የአስፋልት መንገዶች ጋር በማስተሳሰር የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው ኃላፊዋ ገልጸዋል። ዘንድሮ በክልሉ ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ላሉት የገጠር መንገዶች የክልል መንግስት 72 ሚሊዮን ብር የመደበ ሲሆን ማህበራዊ ረዲኤት ትግራይ (ማረት) ደግሞ 80 ሚልዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። በክልሉ ስድስት ዞኖች ውስጥ እየተገነቡ ላሉት መንገዶች በየአከባቢው የሚገኝ ህዝብም የኮንስትራክሽን ቁሳቁሶችን በማቅረብና በጉልበት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ ውስጥ በመገንባት ካሉት ሁሉን አቀፍ የገጠር መንገዶች አብዛኛዎቹ በዚህ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃሉ ብለዋል ። በጸገዴና ወልቃይት ወረዳዎች የተጀመሩ መንገዶች ግን ግንባታቸው የሚጠናቀቀው በቀጣዩ ዓመት መሆኑን ከኃላፊዋ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ። በመንገዶቹ ግንባታ ላይ በ40 ማህበራት የተደራጁ ወጣቶች የስራ አድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በላዕላይ ዓድያቦ ወረዳ ስራው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት በበቃው 15 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ለትራፊክ ክፍት መሆኑ እንዳስደሰታቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል ። በመኪና መንገድ እጦት ምክንያት በወረዳው የሚገኙ እናቶች ቤት ውስጥ እንዲወልዱ ሰለሚገደዱ ለሞት አደጋ ይጋለጡ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ ገብረመድህን ናቸው። ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በዞኑ በቤት ውስጥ ከወለዱት መካከል16 እናቶችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንም ዋና አስተዳዳሪው ገልፀው የመንገዱ አገልግሎት መስጠት መጀመር ችግሩን እንደሚቀርፈውም ገልጸዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች መንገዱ ተመርቆ ለአገልግሎት በመብቃቱ  ደስታቸውን  በሰላማዊ ሰልፍ ገልፀዋል። ደስታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ከገለፁት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ሴት አርሶ አደር ለምለም ምትኩ እንዳሉት የመንገዱ መገንባት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይሰጣል ። ቀደምሲል በመንገድ እጦት ምክንያት በእናቶችና ህጻናት ላይ ይደርስ የነበረውን ሞት እንደሚቀንሰውም ተናግረዋል። “ የመንገዱ አገልግሎት መስጠት የኑሮ ጫናችንን ቀለል ያደርግልናል” ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ ቄስ ተክለሃይማኖት ብርሃነ ናቸው። በትግራይ ክልል 149 የገጠር ቀበሌዎች አሁንም ክረምት ከበጋ የሚያገለግል የገጠር መንገድ እንደሌላቸው ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም