አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የኤሽያ አገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

562

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2012 (ኢዜአ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የኤሽያ አገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ።

አምባሳደር ሬድዋን ውይይቱን ያደረጉት ከባንግላዲሽ፣ ህንድ፣ ስሪላንካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ቻይና አምባሳደሮች ጋር ነው።

በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ የተናጥል ውይይት ማድርጋቸውንም የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

አምባሳደር ሬድዋን ከዚህ በፊት ነዋሪነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እሲያና ኦሽኒያ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ድርጅቶች አምባሳደሮች ጋር አጠቃላይ ትውውቅ አድርገዋል።

የዛሬው የተናጥል ውይይት ደግሞ የተሻለ መተዋወቅ በመፍጠር ቀጣይ ስራዎችን በቅርበትና በትብብር  ለማከናወን ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከኤስያ አገራት ጋር ለረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ የሁለትዮሽ እንዲሁም የባለብዙ ወገን ግንኙነት ያላት መሆኑን አንባሳደር ሬድዋን በውይይቱ ወቅት ገልፅዋል።

ኢትዮጵያ ከአገራት ጋር ያለውን በተለይም የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ባህልና ህዝብ ለህዝብ እንዲሁም የትምህርት እና ስልጠና ትብብር ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላትም አስረድተዋል።

የአገራቱ አምባሳደሮች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለው ምቹ ሁኔታ ለኢንቨስትመንት ጥሩ አማራጭ  መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ዛሬ በነበራቸው የተናጥል ውይይት ከባንግላዲሽ አምባሳደር ሞኒሩል እስላም፣ ከህንድ  አምባሳደር አኑራግ ስራይቫስታቫ ጋር መክረዋል።

በተመሳሳይ ከስሪላንካ አምባሳደር ሱጊሽዋራ ጉናራትና፣ ከደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሊም ሀንሚን እንዲሁም  ከቻይና አምባሳደር ታን ጅያን ጋርም ተወያይተዋል።