በነዳጅ እጥረት የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ ነዋሪዎች መቸገራቸውን ገለጹ

97
ሁመራ፣ የካቲት 4 /2012 (ኢዜአ) በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ሰቲት ሁመራ ከተማ ነዳጅ ከጠፋ 10 ቀናት ስለሆነው በእርሻ ዝግጅትና በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን ባለሃብቶችና ነዋሪዎች ገለጹ። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ደግሞ አንዱ ሌላኛውን ተጠያቂ በማድረግ መግባባት አልቻሉም። የሰቲት ሁመራ ከተማ ነዋሪና ባለሀብት አቶ ዋኘው ጉዑሽ ለኢዜአ እንደገለጹት በነዳጅ እጥረት ምክንያት ለሁለት ሳምንት ያህል የእርሻ ዝግጅት ስራቸው መስተጓጎሉን ገልጸዋል። ‘’ወቅቱ የማሳ ዝግጅት የሚደረግበት በመሆኑ ወደ እርሻ ቦታ ሰራተኞችንና የእርሻ መሳሪያዎች ማመላለስ አልተቻለም '' ብለዋል። በሰሊጥና ማሽላ አምራችነቱ የሚታወቀው የቃፍታ ሁመራ አካባቢ ወቅቱን ጠብቆ የማሳ ዝግጅት ካልተደረገ በምርታማነቱ ላይ ተፅእኖ ስለሚፈጥር የነዳጅ ችግሩ በፍጥነት እንዲፈታ ጠይቀዋል። በከተማው የነዳጅ እጥረት በማጋጠሙ ከሽሬ ከተማ ድረስ ሰውን በመላክ በውድ ዋጋ ገዝተው ለመጠቀም መገደዳቸውን የገለፁት ደግሞ  የከባድ ጭነት ተሽካርካሪ ሾፌር አቶ መሀመድ ሰይድ ናቸው። የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ሾፌር አከቦም ገብረእግዝአብሄር እንደተናገረው በከተማው እንደ አሁኑ የከፋ የነዳጅ እጥረት አጋጥሞ አያውቅም። አንድ የናፍጣ ሊትር በ19 ብር የሚገዛው በጥቁር ገበያ በ35 ብር ለመግዛት ተገደዋል። በቃፍታ ሁመራ ወረዳ የባዕከር ከተማ ነዋሪ አቶ በሪሁ ሀይሉ በበኩላቸው በነዳጅ እጥረት ምክንያት የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ ገድቦታል። በዚህም ከሁመራ ወደ ሽሬ እንዳስላሴ ከተማ 50 ብር የነበረው የአንድ ኩንታል እህል የጭነት ዋጋ ወደ 80 ከፍ ብሏ። በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት አንዲሰጡ የተጠየቁት የከተማው ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊና የክልሉ ንግድ ኢንዱስቱሪና  ከተማ ልማት ቢሮ የንግድ ዳይሬክተር አንዱ ሌላውን ተጠያቂ ከማድረግ የዘለለ መፈትሔ የሚያመላክት ምላሽ አልሰጡም። በሰቲት ሁመራ ከተማ የንግድ ኢንዳስትሪና ከተማ ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ዳንኤል ፀጋይ በበኩላቸው እንዳሉት የእጥረቱ መንስኤ አቅርቦቱና ፍላጎቱ አለመጣጣም መሆኑን ተናግረዋል። ባለፉት ሶስት ወራት በከተማው ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ የነዳጅ ስርጭት መቆራረጥ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው  በአሁኑ ወቅት የነዳጅ  ማደያዎች በነዳጅ እጥረት ምክንያት ስራ ማቆማቸውን እውነት መሆኑን አስረድተዋል:: በቃፍታ ሁመራ ከሚካሄደው ዘመናዊ የእርሻ ስራዎች ጋር በተያያዘ በከተማው በቀን 48 ሺህ ሊትር ነዳጅ ያስፈልጋል ። ፍላጎቱን መሰረት ያደረገ የነዳጅ አቅርቦት እንዲቀርብላቸው በተደጋጋሚ ለክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ፅህፈት ቤት በተደጋጋሚ  ቢጠይቁም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አቶ ዳንኤል ተናግረዋል። የክልሉ ንግድ ኢንዱስቱሪና  ከተማ ልማት ቢሮ የንግድ ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረመድህን ተወልደ በበኩላቸው የነዳጅ እጥረቱ የተከሰተው የሰቲት ሁመራ ከተማ ንግድ ኢንዱስቱሪና ከተማ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች የመጠባበቂያ ነዳጅ እስኪያልቅ ድረስ ጥያቄ ባለማቅረባቸው ነው። በከተማው የነዳጅ መጠባበቂያ ክምችቱ 30 በመቶ ሲደርስ ተጨማሪ ነዳጅ መጠየቅ ሲገባው ሙሉ በሙሉ እስኪሟጠጥ ድረስ ጥያቄ አላቀረበም ብለዋል። የከተማው ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ግን ጥያቄ አልቀረበም የተባለው ተገቢነት ስለሌላው በአቶ ገብረመድህን ወቀሳ አልስማም ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም