ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ አከናውናለች

67
አዲስ አበባ የካቲት 4 /2012 (ኢዜአ) ከ33ኛው የአፍሪካ ህብረት  የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወኗን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት አስታወቀ። የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የመሪዎቹ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኮሚቴ ተዋቅሮ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል። በመሆኑም አዲስ አበባ ከ10 ሺህ የሚበልጡ እንግዶችን በመቀበል በጥሩ ሁኔታ ተስተናግደው እንዲሸኙ ተደርጓል። ከጉባኤው በተጓዳኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተላያዩ አገራት መሪዎች ጋር እንዲወያዩ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት ምክክር ያደረጉባቸውን ሀገራት ተጨባጭ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር በማስማማት ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ አከናውነዋል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናን በሚመከት ባደረጉት ምክክርም በተለይ የጎረቤት ደቡብ ሱዳን አገረ መንግስት ግንባታ በሰላም በሚጠናቀቅበት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መወያየታቸውንም ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ባለፈ የአፍሪካ ቀንድ ከሳህል ቀጠና ጋር በሚተሳሰርበት ሁኔታ ላይ ከአልጀሪያው ፕሬዝዳንት አብዱልመጂድ ተቦን ጋር ተወያይተዋል። ኢትዮጵያና አልጀሪያ በኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂና ባህል ዘርፎች በትብብር በሚሰሩበት ሁኔታም መሪዎቹ መምከራቸውን ነው አቶ ንጉሱ የተናገሩት። በኢትዮጵያን ታሪክ ወስጥ የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን አጣምሮ የያዘውን "አንድነትፓርክ" በመጠቀም የገጽታ ግንባታና ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ መከናወኑንም አቶ ንጉሱ አክለዋል። "ፓርኩን ለሌሎች አፍሪካ አገራት ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉ" በጉብኝቱ የተሳተፉ መሪዎች አስተያየት መስጠታቸውንም አስታውሰዋል። በጉባኤው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ተነስተው ውጤታማ ውይይት የተደረገባቸው መሆኑንም  ጠቅሰዋል። ለ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ስኬታማነት ከአቀባበል እስከ አሸኛኘት ጉልህ አስተዋጽኦ ላደረገው የአዲስ አበባ ነዋሪም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም