በሐረሪ ክልል የግጭት መንስኤና ወንጀሎችን ለመከላከል እየተሰራ ነው

90

ሐረር፤ የካቲት 3 /2012 (ኢዜአ)በሐረሪ ክልል ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ እንቅስቃሴዎችና ወንጀሎችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት ገለጸ።

የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት የስራ አፈጻጸም ግምገማ በሐረር ከተማ ተካሄዷል።

የምክር ቤቱ አባልና የሐረሪ ክልል ፖሊስ የወንጀል መከላከልና የትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክተር ኮማንደር አብዲ ኢብራሂም በግምገማው መድረክ እንዳሉት በአከባቢው የሚስተዋሉ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ እየተሰራ ነው።

በተለይ ባለፉት ሁለት ወራት በመሬት ወረራና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ 200 የሚጠጉ ግለሰቦችን መያዛቸውን አመልክተዋል።

በጥምቀት በዓሉ ወቅት ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 168 ግለሰቦች መካከል 138 ጉዳያቸው ተጣርቶ መለቀቃቸውንና ተዘረፈው ከነበሩ 18 የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች መካከል 17 መመለሳቸውን ጠቅሰዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል በተከናወነው ስራ ግምቱ 447ሺህ ብር የሚገመቱ እቃዎች ተይዘዋል።

በከተማው ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመከላከል በተደረገው ጥረትም ከአራት ሺህ ሊትር በላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር ተያይዞ 86 ኮብላዮችና 11 አስኮብላዮች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንጃ ፍቃድና የሰሌዳ ቁጥር ሳይኖራቸው ሲያሽከረክሩ የተገኙ 118 ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ስርዓት እንዲይዙ ተደርጓል።

በጥምቀት በዓል ወቅት በጸጥታ ችግር ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች በአካባቢ ህብረተሰብ ድጋፍ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የክልሉ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ናስር ዩያ ናቸው።

" የህዝቡ የአብሮነት እሴት እንዲጎለብት ከማድረግ አንጻር በተለይ አመራሩ በትኩረት መንቀሳቀስ ይገባል "ብለዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ረመዳን ኡመር በበኩላቸው ባለፉት ወራት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ቢሆኑም ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጎልበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በየአካባቢው የግጭት መንስኤ የሆኑ እንቅስቃሴዎችና ወንጀሎችን ህዝብን በማሳተፍ ከምንጩ ለማድረቅ የተቀናጀ ስራ ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የህግ የበላይነት ማስከበርና ሰላምን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከምስራቅ ዕዝ መከላከያ የመጡት ሻለቃ ተስፉ ዝምበላቸው ናቸው።

በተለይ በክልሉ ህግና ስርዓትን ከማስከበር አንጻር ትራፊክ ፖሊሶች በተሻለ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል።

በመድረኩ የምክር ቤቱ አባላት የሆኑ የክልሉና የፌዴራል የጸጥታ አካላት፣ የምስራቅ ዕዝ መከላከያና የወረዳ አስተዳደር አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም