ለ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን አርሶ አሮች ቋሚ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተሰጠ

118

ባህርዳር ኢዜአ የካቲት 3 /2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ለሚበልጡ አርሶ አደሮች ቋሚ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በመስጠት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ማስቻሉን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ ።

በቀጣይ ዓመታት በ165 ሚሊዮን ዶላር ቋሚ የይዞታ ደብተር መስጠት የሚያስችል የካልም ፕሮጀክት ውይይት በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አያያዝና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ትግስቱ ገብረመስቀል እንደገለጹት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአርሶ አደሩ እጅ ከ50 ሚሊዮን በላይ ማሳ ይገኛል።

ከእነዚህ ውስጥ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው ስራ  በ20 ሚሊዮን ማሳዎች ላይ የቅየሳና የምዝገባ ስራዎች መከናወኑንና 15 ሚሊዮን ለሚሆኑት ደግሞ 2ኛ ደረጃ ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠት መቻሉን ገልፀዋል።

ይህም ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚበልጡ አርሶ አደሮች ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኙ በማድረግ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አግዟል ብለዋል።

አቶ ትግስቱ  እንደገለጹት ቋሚ ደብተር የተሰጣቸው አርሶ አደሮችም ማሳቸውን በዋስትና በማስያዝ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ 428 ሚሊዮን ብር ብድር ወስደው ከግብርና ውጭ በሆኑ የገቢ ማስገኛ የስራ መስኮች መሰማራት ችለዋል ።

ከዓለም ባንክ በተገኘ 165 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ድጋፍም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ካልም በተባለ ፕሮጀክት በ8 ክልሎች  እንደሚተገበር ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ በ280 ወረዳዎች 2 ሚሊዮን የሚጠጉ የአርሶ አደሮች ማሳን በመቀየስና በመመዝገብ ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኙ  ይደረጋል ብለዋል።

የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ ዳምጤ በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት ስምንት ዓመታት ለ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ይዞታዎች ሰርተፍኬት ተሰጥቷል።

አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ሁለተኛ ደረጃ ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይ አምስት ዓመታትም ለሁሉም አርሶ አደሮች በካርታ የተደገፈ ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኙ ይሰራል ብለዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ አባይ ካሴ በውይይቱ እንዳሉት የፕሮጀክቱ መተግበር የመሬት አስተዳደር ስርዓቱ  እንዲዘምንና ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ክርክሮች እንዲቀንሱ ያደርጋል።

ፍርድ ቤቶች ከሚመለከቷቸው ክርክሮች ውስጥ 90 በመቶው የሚሆነው የመሬት ጉዳይ ሲሆን በተደራጀ መልኩ የተያዘ መረጃ ባለመኖሩ  ለውሳኔ ሲቸገሩ ቆይተዋል ነው ያሉት።

ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠት ከጀመረ ወዲህ ጫናው በመጠኑም ቢሆን እየቀነሰ እንደመጣ  አስረድተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው ዞኖችና ወረዳዎች፣ ከክልልና ከግብርና ሚኒስቴር የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።