የተጀመረው የአንድነት ጉዞ ለማስቀጠል ከአዲሱ አመራር ብዙ እንደሚጠብቁ በሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

63
ሀዋሳ 20/ 2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀመሩትን የአንድነትና የመደመር ጉዞ ለማስቀጠል ከአዲሱ የደኢህዴን ሊቀመንበር ብዙ እንደሚጠብቁ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከደኢህዴን ሊቀመንበርነት በፈቃዳቸው መልቀቃቸው ወጣቱ እያቀረበ ካለው የለውጥ ጥያቄ በተገቢው ሰዓት የተሰጠ ምላሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አማን ኑረዲን እንደተናገሩት በተለይ ወጣቱ ከስራ አጥነት ጋር በተያያዘ ትግል ሲያደርግ  ቆይቷል፡፡ ይህንን  ተከትሎ ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ ካደረገ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር አብይ አህመድ እያከናወኗቸው ያሉት ተግባራት ተቀባይነት እንዳስገኘላቸው ገልጸዋል፡፡ በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ደኢህዴን ራሱን ለመለወጥ በማሳብ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በፈቃዳቸው ሊቀመንበርነታቸውን መልቀቃቸው ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እየመጣ ካለው አዲስ አመራር ብዙ እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዮናታን በላቸው በበኩላቸው ስልጣን የቅብብሎሽ እንጂ የዕድሜ ልክ ሳይሆን አንዱ ለአንዱ እያቀበለ የሚሄድበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህዘቡ አሁን የሚፈልገውን ለውጥ ለማስተናገድ የተሻለ ሰው ቢመራው በሚል አቶ ሺፈራው መልቀቃቸው ተገቢ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "  በሀገር ደረጃ የመጣው አዲስ ለውጥ የተሻለ ነገር እንዳመጣ ህዝቡ እያየ ነው"ብለዋል፡፡ በከተማው የመናኸሪያ አካባቢ ነዋሪው  ወጣት ወልደአማኑኤል ቅባቱ በሰጠው አስተያየት  ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር  ከሆኑ ወዲህ  ተስፋ ሰጪ ለውጦች በማየቱ መደሰቱን ገልጿል፡፡ አዲሱ አመራር ሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተቻችለው በአንድነትና በፍቅር እንዲኖሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው የገለጸው ደግሞ  በንግድ ስራ የተሰማራው ወጣት አብዱራዛቅ ውጅራ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም