ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን የማዘመን ስራ እየተሰራ ነው

109
አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 3/2012 በአዲስ አበባ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ፡፡ የፌዴራል የስነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በመዲናዋ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር በተመለከተ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል። በውይይቱም በአዲስ አበባ የሚስተዋለው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ለከተማ አስተዳደሩ ፈተና እንደሆነም ተመልክቷል። በጸረ-ሙስና ኮሚሽን የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ከፍያለው እንዳሉት የመረጃ አያያዝ ማነስ፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት ችግሮች፣ የሕግ ስርዓቶች አለመከበርና ከመልሶ ማልማት ጋር ተያይዞ ያለው አሰራር ለመሬት ወረራው መስፋፋት ምክንያቶች ሆነዋል። "በዚህም በከተማ አስተዳደሩ መሬት ለሙስናና ብልሹ አሰራር፣ ለፖለቲካ፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መከሰት ዋነኛ መንስዔ እየሆነ መጥቷል" ሲሉም ተናግረዋል። በከተማ አስተዳዳሩ ከሚገኙ 55 የመንግስት ተቋማት መካከል 17ቱ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከመሬት ጋር በተገናኘ ስራቸውን የሚከውኑ ቢሆንም የመሬት ወረራውን ማስቀረት ግን አልተቻላቸውም ብለዋል። በመሆኑም "የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ጥረት መደረግ ይኖርበታል" ነው ያሉት። ችግሩን ለመቅረፍ የተጠያቂነት ስርዓቱ ከዚህ በበለጠ መጎልበት እንዳለበትም አመልክተዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል መጋቤ ካህናት ሃይለስላሴ ዘማርያም በሰጡት አስተያየት የከተማ አስተዳደሩ ሕገ-ወጥ ግንባታዎች ከመካሄዳቸው በፊት ቅድመ መከላከል ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩ መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኤልያስ ዘርጋውም ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ተያያዥ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። "በመዲናዋ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የማዘመን ስራ እየተሰራ ይገኛል" ሲሉ ጠቅሰዋል። የመሬት ይዞታዎችን አሰራር ከወረቀት የጸዳና ዲጂታላይዝ ለማድረግ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰራ መሆኑን በማስታወስ። በመሬት ማኔጅመንት ዘርፍ ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረውን የአደረጃጃት ችግር በመፍታት ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል። ለመሬት ወረራው መባባስ የመረጃዎች በአግባቡ አለመያዝ ችግር እንደነበር የጠቆሙት ደግሞ የአዲስ አበባ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ትርሃስ ሃይለስላሴ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ባዶ ቦታዎችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረውን ሕገ-ወጥ ወራራ ለመከላከል አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል። የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የሥራ አጥነት ማሻቀብ፣ የመኖሪያ ቤት ችግርና የከተሞች ወሰን አለመኖር በአፍሪካ ከተሞች ለሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸው በውይይቱ ላይ ተመልክቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም