የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያበረታታ አማካሪ ካውንስል ተመሰረተ

57
አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 3/2012  የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚያስችል የታመነበት አማካሪ ካውንስል ዛሬ ተመሰረተ። ካውንስሉ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሞተር መሆኑን በተግባር ለማረጋገጥ ይረዳልም ተብሏል። የልማት ዕቅዶችና ፕሮግራሞች ሂደት ውስጥ በመሳተፍ የግሉን ዘርፍ የሚመለከቱ የመንግስት አሰራሮችና መመሪያዎችንም ይገመግማል። ሃሳብና አማራጮችን የሚጠቁምና የዘርፉን ተሳትፎ የሚያበረታታ እንዲሁም በግሉ ዘርፍና በዕቅድና ፖሊሲ አውጪዎች መካከል የመረጃ ፍሰትን የሚያሳልጡ መዋቅሮች የመዘርጋት ተግባራትን ይከውናልም ተብሏል። ካውንስሉ ሲመሰረት በኢትዮጵያ በግሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሚና እየተጫወቱ ካሉ የንግድ ተቋማት፣ አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም ትላልቅ ኩባንያዎችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ኃላፊዎች የተውጣጡ ዕጩ አባላት ተገኝተዋል። ይህ ካውንስል ከፕላንና ልማት ኮሚሽን ጋር በቅርበት የሚሰራና የግሉን ዘርፍ በመወከል የሚንቀሳቀስ እንደሆነ ታውቋል። የፕላንና ልማት ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋ በምስረታው ወቅት እንዳሉት የግሉ ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ዕቅድ ሲታቀድ የቆየ ቢሆንም በትግበራ ረገድ ግን ሚናውን እንዳልተወጣ ነው የሚታየው። የኃይል አቅርቦትና መሰል መሰረተ ልማት በሚፈለገው መጠን መቅረብ አለመቻልና የአገር ውስጥ ጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት የግሉ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ያህል ኢኮኖሚውን እንዳይደግፍ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውንም ኮሚሽነሯ አንስተዋል። መንግስት እያካሄዳቸው ካሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች አንዱ የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ተሳትፎ ማሳደግ መሆኑን ገልፀው እየተዘጋጀ ባለው የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድም ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል። የግሉ ዘርፍ በዋናነት አተኩሮ ሲሰራ የቆየው በኮንስትራክሽንና በአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰዋል። የካውንስሉ መመስረት የግሉን ዘርፍ የተመለከቱ እቅዶች በመንግስት ሲታቀዱ በተናጠል መሆኑ ቀርቶ በትብብር እንዲሆን ያስችላል፤ እቅዶች እንዳይተገበሩ የሚያደርጉ አሳሪ ህጎችንም በመለየት በትብብርና ቅንጅት እቅዶችን ለመተግበር ይረዳል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም