ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አፈቃቀድ መከታተያ አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን ገለጸ

95
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አፈቃቀድ ላይ ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጥ አዲስ አሰራር ዘርግቻለው አለ። በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከመኖሩ ባለፈ ከውጭ እቃ ለሚያመጡ ባለሃብቶች የሚፈቀድበት ቅደም ተከተልም ችግር እንዳለበት ቅሬታዎች ይሰማሉ። የተዘረጋው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አዲስ አሰራርም የውጭ ምንዛሪ ከምዝገባ ጀምሮ እስኪፈቀድ ድረስ ለማን እንደተፈቀደ ብሔራዊ ባንክና የባንኮች የበላይ ኃላፊዎች መከታተል የሚችሉበት ነው ተብሏል። አሰራሩም ለአገር ከሚሰጠው ጠቀሜታ አስፈላጊነት ረገድ ታይቶ አንገብጋቢ በተባሉ የነዳጅ፣ የማዳበሪያ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓትና መሳሪያዎች እንዲሁም ለመድሃኒት አስመጪዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተፈቀደ መሆኑን ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው። በባንኩ የውጭ ምንዛሪ ክትትልና ሪዘርቭ አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ የኔሃሳብ ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት አሰራሩ ውስን የሆነውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ለመጠቀም ያግዛል። በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም መኖሩን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ በባንኮች የውጭ ምንዛሪ አፈቃቀድ ስርዓታቸው የተለያየ መሆኑን ነው የገለጹት። ይጠቀሙበት የነበረው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አሰራር ክፍተት እንደነበረበት የገለጹት ወይዘሮ የኔሃሳብ፤ ለአብነትም በምዝገባ ስርዓቱ ላይ አስመጪዎችን አለመመዝገብና የተቆራረጠ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አሰራር መጠቀምን ጠቅሰዋል። እነዚህንና ሌሎች በውጭ ምንዛሪ አፈቃቀድ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል ብሔራዊ ባንክ ከግንቦት ወር ጀምሮ አዲስ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አሰራር ተግባራዊ አድርጓል። አሰራሩ የትኛውም ባንክ ላይ ማን መቼ እንደተመዘገበ፣ ለምን እንደጠየቀና መቼ እንደተፈቀደ መከታተል ስለሚያስችል የነበሩ የፍትሃዊነት ችግሮች ይፈታሉ ብለዋል። በተጨማሪም ባንኮች በየጊዜው የፈቀዱትን የውጭ ምንዛሪ ሪፖርት ማድረግ ሳይጠበቅባቸው ከሲስተሙ ማግኘት እንደሚያስችልም ገልጸዋል። ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ቅድሚያ ለማይሰጣቸው ዘርፎች ቅድሚያ የመስጠት አሰራሮች እንደነበሩ በመግለጽ አዲስ የተዘረጋው አሰራር እራሱ ከፋፍሎ የሚያስቀምጥ ነው ብለዋል። እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ ከተፈቀደላቸው በ15 ቀን ውስጥ አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት የውጭ ምንዛሪውን ወስደው ሊጠቀሙበት ይገባል። አሰራሩ አስመጪዎች በአንድ ጊዜ ተመሳሳይ ጥያቄ ለተለያዩ ባንኮች እንዳያስገቡም መቆጣጠር የሚያስችል ሲሆን፤ ውስን የሆነውን የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች መዋሉን ለመቆጣጠር ያስችላል። በሚወጡ መመሪያዎች ላይ  አስመጪዎች እኩል ግንዛቤ ኖሯቸው መብትና ግዴታቸውን እንዲለዩ በባንኮች እንዲሰራጭ ተደርጓል። ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም መመሪያ አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ ሲሆን፤ መመሪያውን በትክክል የማይተገብሩ ባንኮች እንደጥፋት አይነቱ እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ በወንጀል እንዲጠየቁ ያደረጋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም