33ኛ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ትናንት ሌሊት ላይ ተጠናቀቀ

406

33ኛ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ትናንት ሌሊት ላይ በ10 ሰዓት ተጠናቀቀ።

33ኛው የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ”ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የጦር መሳሪያ ድምጽን ማጥፋት” በሚል ርዕስ ለሁለት ቀናት ሲያካሂዱት የቆየው ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ መቋጫውን አግኝቷል።

በአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ጉባኤ የጸደቀውን የተለያዩ የኅብረቱ ተቋማት ምርጫን በተመለከተም የመሪዎቹ ጉባኤ አጽድቆታል።

 በዚህም መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ 10 አገሮች የተመረጡበትን አዲሱን የኅብረቱ የሰላምና የደህንነት ምክር ቤት አባላትና ሌሎችም ተዛማች የአባላት ሹመትን አጽድቀዋል።

ሠላምና ፀጥታ

 መሪዎቹ ባደረጉት ስብሰባ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥና የየአገሮቹ ዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ሁሉም አባል አገሮች በዚህ ረገድ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት አቋም ይዘዋል።

አሁንም ቢሆን በመካከለኛው አፍሪካ፣ በሊቢያ፣ ቻድ ሸለቆ አካባቢ፣ በምዕራባዊ ሳህል፣ በካሜሮን፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን የጸጥታ ችግሮች መኖራቸውን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

በተለይም ሊቢያን በተመለከተ የአፍሪካ ኅብረት ሚና አናሳ የሆነበትና ሌሎች የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች በውክልና ጦርነት ተሳታፊ እየሆኑ ነው የሚል ቅሬታም እየቀረበ ነው።

 እንዲያውም በተያዘው የፈረንጆች ዓመት የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የጸጥታ ችግር ሊቀሰቀስ እንደሚችልና የጦር መሳሪያ ድምጽ ጎላ ብሎ ሊሰማ እንደሚችል ከወዲሁ ግምት ተሰጥቷል።

  በተለይም ደግሞ በአገሪቱ ምርጫ የሚካሄድባቸው አገሮች መኖራቸውን ተከትሎ የድህረ-ምርጫ ግጭት ሊኖር እንደሚችል ነው ትንበያዎች እየወጡ ያሉት።

  ለአብነትም በአፍሪካ ላይ የሚሰራው የደህንነት ጥናት ተቋም እንዳስታወቀው፤ በአፍሪካ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ 21 ሺህ 600 ስፍራዎች ላይ በመሳሪያ የታገዘ ግጭቶች ተመዝግቧል።

ይህም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከነበረው 15 ሺህ 874 የ36 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ጠቁሞ፤ ዓመቱ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ሊታይበት እንደሚችል ነው ግምቱን ያስቀመጠው።

እነዚህንም የጸጥታ ችግሮች ከአሁኑ እልባት በመስጠትና ለሌሎችም ችግሮች ትኩረት በመስጠት የኅብረቱን የዓመቱ አጀንዳ ከግብ ማድረስ እንደሚገባ መሪዎቹ አጽንጾት እንደሰጡት ተናግረዋል።

በአህጉሪቱ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት ህብረቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን አካሄድ መለወጥና አዲስ ሥልት መቀየስ እንዳለበት ተጠቁሟል።

ነጻ የንግድ ቀጠና

 ነጻ የንግድ ቀጠና በአሁኑ ወቅት 28 አገሮች እንዳጸደቁትና በመጪው ሐምሌ ወር ላይ ወደ ሥራ ለማስገባት አፍሪካ ኅብረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

 እስከ ግንቦት ወር መጨረሻም ሥምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚሰራና ተግባራዊ ሲሆንም ለአህጉሪቱ የንግድ ሥርዓት አብርክቶው የጎላ ነው ተብሏል።

  በነጻ የንግድ ቀጠናው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ የሚሆነው የአፍሪካ ሕዝብና 3 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር ለያዘው የአህጉሪቱ ጠቅላላ አገራዊ ምርት ነጻ የሰዎችና የካፒታል ዝውውር ይፈቅዳል ተብሏል።

 ይህንንም ሥምምነትም አባል አገሮች በቁርጠኝነት በመስራትና በተያዘለት የጊዜ ገደብ በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ኮሚሽነሩ ሙሳ ፋኪ ማረጋገጫቸውን የሰጡት።

ሥምምነቱም ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ አጠቃላይ የአህጉሪቱ ጠቅላላ ምርትና የሥራ እድል ፈጠራ ከፍ ያደርገዋል ተብሏል።

 የአፍሪካ አገሮች የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ደግሞ በ24 በመቶ ከፍ እንሚያደርገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ያጠናው ጥናት ያመላክታል።

 ሴቶችና ሕጻናትና ወጣቶች

በአፍሪካ ሴቶችን በተለይም በኢኮኖሚና በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከአገሮች የተናጠል ሥራ ጎን ለጎን በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል።

በተለይም የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀ-መንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሴቶች በየአገራቱ የመንግሥት አዋቃቀር ውስጥ ፍትሃዊ ስፍራቸውን እንዲያገኙ ለመስራት ቃል ገብተዋል።

በአሁኑ ወቅት ግጭትና የጸጥታ ቀውስ በሚታይበት የአህጉሪቱ ክፍሎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትም የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ኅብረቱ በጉባኤው አጽንጾት ሰጥቶታል።

የህጻናትን ጉልበት ብዘበዛ ለማስቀረትና ሰብዓዊ መብታቸውን እንዲከበር አገሮች በትኩረት እንደሚሰሩና ኅብረቱም ከጎናቸው እንደሚቆም በስብሰባው ተጠቅሷል።

በአፍሪካ አጠቃላይ ሕዝብ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጣት ሲሆን ይህንን የሰው ኃይል በማሰልጠንና በማስተማር አህጉሪቱን ለመለወጥ እንሰደሚሰራ ተገልጿል።

ከዛም ባለፈ ሰፊ የሥራ እድል ማዘጋጀት እንደሚገባም ተጠቁሟል።

 ስደትና ጤና
በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከልና ለመቋቋም ኅብረቱ ከአባል አገሮች ጋር በመሆን ሁሉን አቀፍ የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን በጉባኤው ተገልጿል።

በተለይም ለቫይረሱ ተጋላጭና ወደ ቻይና ቀጥታ በረራ ያላቸው 15 አገሮች ተለይተው የምርመራና ተያያዝ የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ የአቅም ማጎልበት ሥልጠና እየተሰጣቸው ነው።

እስካሁንም በአህጉሪቱ ቫይረሱ አልተገኘም፤ ነገር ግን እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑንም በዚሁ ጉባኤ ተጠቅሷል።